አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም በእውነት እናምናለን ልመናዋ ክብሯ የልጅዋም ቸርነት ከሁላችን ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን። አምላክን የወለደች በውስጥ ከሁላችን በአፍኣ ንጽሕት የምትሆን የብርሃን እናቱ እመቤታችን እግዝእትነ ማርያም በሰኔ ሐያ አንድ ቀን በጎልጎታ ይኸውም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መካነ መቃብር በሚሆን እንዲህ ስትል የጸለየችው ጸሎት ይህ ነው። ልጄ ወዳጄ ጌታዬ አምላኬና ንጉሤ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ሰውን ለማዳን ስትል በፈቃድህ ከኔ ተወልደህ ጡቶቼንም ጠብተህ በግዕዘ ሕፃናት ብታድግ ሰማይና ምድር አይችሉህም እኮን። የዓለም ዳርቻዎች አይወስኑህም ልተሸከምህ አትችልም፤ ቀላያት አብሕርትም ከጥልቀታቸው የተነሣ የክረምት ማዕበልም፤ በእፍኝህ አየመሉም ኃይላት መላእክትም ቢሆኑ ወደአንተ ሊቀርቡ አይችሉም አቤቱ እኔ እናትህ ገረድህ የምሆን በማኅፀኔ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ተሸክሜሃለሁና ጡቶቼንም አራት ዓመት እየጠባህ አድገሃልና እለምንሃለሁ እማልድሃለሁ። ሄሮድስ በምቀኝነት ሊገድልህ በፈለገ ጊዜ አንተን በጀርባዬ አዝዬ አራት ዓመት ከአንዱ ሀገር ወደ አንዱ ሀገር ተሰድጃለሁና አቤቱ ጌታዬና አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ጸሎቴንና ልመናዬን ስማኝ። አቤቱ ማኅፀኔን ዓለም አድርገህ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን የተሸከምኩህን አቤቱ በቍርና በብርድ ወራት በቤተ ልሔም ከኔ መወለድህን አስብ። አቤቱ ከአንተ ጋራ ከሀገር ወደ ሀገር መሰደዴን ስለአንተም የደረሰብኝን ጭንቅና መከራ ረሀብና ጥም አስብ፤ የምለምንህም ለደጋጐች ለጻድቃን ብቻ አይደለም፤ በዚህ ዓለም ሳሉ ስሜን ለሚጠሩ መታሰቢያዬን ለሚያደርጉ በአማላጅነቴ ለሚተማመኑ ኃጥኣንም ነው እንጂ፤ አቤቱ ጸሎቴንና ልመናዬን አስተውል፤ ከአንተ ዘንድ የምሻውን የቃሌን ልመና ትሰማኝ ዘንድ የልቦናዬንም ሀሳብ ትፈጽምልኝ ዘንድ። በዚህ ዕለትና በዚችም ሰዓት ዐሥራ ሁለት የብርሃን መላእክትን ሁለት የይቅርታ መላእክትን፤ ሃያ ዐራት የምሕረት መላእክትን ከኔ ጋር ቁመው የልቡናዬን ይፈጽሙልኝ ዘንድ ላክልኝ ካንተ ዘንድ የምሻውንም ቸርነትህን አታርቅብኝ። ልጄ ወዳጄ ሆይ፤ ዓለም ሳይፈጠር አስቀድሞ ከአንተ ጋር በነበረ እግዚአብሔር አብ በባሕርይ አባትህ ቃል ኪዳን ትገባልኝ ዘንድ እማልድሃለሁ። ልጄ ወዳጄ ሆይ፤ሰማይና ምድር ተራሮችና ኮረብቶች፤ ሰውና መላእክት ፀሐይ ጨረቃና ከዋክብት ሳይፈጠሩ ቀንና ሌሊት ሳይለዩ በነበረ በእግዚአብሔር ስምህ ቃል ኪዳን ትገባልኝ ዘንድ እማልድሃለሁ። ልጄ ወዳጄ ሆይ፤ የአብ የባሕርይ ሕይወቱ የሆነ ከአብ በተገኘ የአንተም የባሕርይ ሕይወትህ በሆነ ከአንተ ጋር የተካከለ በጰራቅሊጦስ መንፈስ ቅዱስ ከኮከብ መውጣት በፊት ከአንተ ጋር በነበረ አሁንም ያለ ለዘለዓለምም የሚኖር በአብና በመንፈስ ቅዱስ ቃል ኪዳን ትገባልኝ ዘንድ እማልድሃለሁ። ልጄ ወዳጄ ሆይ፤ ሰማይ ምድር ሊወስኑህ የማይቻላቸው አንተን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በተሸከመችህ ማኅፀኔ ቃል ኪዳን ትገባልኝ ዘንድ እማልድሃለሁ። ልጄ ወዳጄ ሆይ፤ እለ ብዙኃት አዕይንቲሆሙ የተባሉ ፀወርተ መንበርህ ኪሩቤል በፍርሐትና በረዓድ እየተንቀጠቀጡ መንበርህን የሚሸከሙ አንተ ባዘለችህ ጀርባዬ ቃል ኪዳን ትገባልኝ ዘንድ እማልድሃለሁ። ልጄ ወዳጄ ሆይ፤ ከርጉም ሄሮድስ ፊት ሸሽተን ወደ ግብፅ አካባቢ እስክንደርስ ድረስ በደረሰብኝ ረኃብና ጥም ቃል ኪዳን ትገባልኝ ዘንድ እማልድሃለሁ። ልጄ ወዳጄ ሆይ፤ አንተን ይገድሉሃል እያልኩ ሳስብ ከዓይኖቼ እንደሰን ውሀ እየፈሰሱ በክብርት ሥጋህ ላይ በወረዱት ዕንባዎቼ ቃል ኪዳን ትገባልኝ ዘንድ እማልድሃለሁ። ልጄ ወዳጄ ሆይ፤ ምን ምን ሊቀርብህ የማይችል አንተን በሳሙ ከንፈሮቼ ቃል ኪዳን ትገባልኝ ዘንድ እማልድሃለሁ። ልጄ ወዳጄ ሆይ፤ ከአንተ ጋር ቃል ለቃል በተነጋገረ አንደበቴ፤ ሱራፌል ኪሩቤል ድምፅህን ሰምተው ፀንተው ለመቆም የማይቻላቸው ጥዑማት ቃላትህን በሰሙ ጆሮቼ ሰላሳ ሦስት ዓመት ከአውራጃ ወደ አውራጃ ከአንተ ጋራ በተመላለሱ እግሮቼ ቃል ኪዳን ትገባልኝ ዘንድ እማልድሃለሁ። ልጄ ወዳጄ ሆይ፤ ልብሱ እሳት ክዳኑ እሳት እየተባልክ የምትመሰገን አንተ፤ እሳተ መለኮት ስትሆን በጨርቅ ተጠቅልለህ በተጣልክበት ዋሻ (በረት) ቃል ኪዳን ትገባልኝ ዘንድ እማልድሃለሁ። ልጄ ወዳጄ ሆይ፤ መላከ ምክርህ በሆነ ቅዱስ ሚካኤል አንተን በክብር እወልድ ዘንድ የመወለድክን ዜና (ምሥራች) በነገረኝ በቅዱስ ገብርኤል ቃል ኪዳን ትገባልኝ ዘንድ እማልድሃለሁ። ልጄ ወዳጄ ሆይ፤ በምጥ የተያዙትን ሴቶች ማኅፀን ይፈታ ዘንድ ሥልጣን በሰጠኸው በቅዱስ ሩፋኤል ቃል ኪዳን ትገባልኝ ዘንድ እማልድሃለሁ። ልጄ ወዳጄ ሆይ፤ የሰላምና የደኅንነት መልአክ በሆነ በዑራኤል መልአክ ቃል ኪዳን ትገባልኝ ዘንድ እማልድሃለሁ። ልጄ ወዳጄ ሆይ፤ ያዘኑትን የሚያረጋጋ በሰዳካኤል መልአክ፤ ጻድቅና ትሑት በሆነ በሰላትያል መልአክ ቃል ኪዳን ትገባልኝ ዘንድ እማልድሃለሁ። ልጄ ወዳጄ ሆይ፤ ዙፋንህን በሚሸከሙ ዐርባ ዐራቱ እንስሳ ኪሩቤል ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር እያሉ አነዋዋርህን በማመስገን መንበርህን በሚያጥኑ ሃያ ዐራቱ ካህናተ ሰማይ ሱራፌል ቃል ኪዳን ትገባልኝ ዘንድ እማልድሃለሁ። ልጄ ወዳጄ ሆይ፤ ተልእኮታቸውን ለማፋጠን በሚፋጠኑ ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት ቃል ኪዳን ትገባልኝ ዘንድ እማልድሃለሁ። ልጄ ወዳጄ ሆይ፤ እልፍ ሆነው በፊትህ በሚቆሙ እልፍ ሆነው በኋላህ በሚቆሙ እልፍ ሆነው በቀኝህ በሚቆሙ እልፍ ሆነው በግራህ በሚቆሙ መላእክት ቃል ኪዳን ትገባልኝ ዘንድ እማልድሃለሁ። ልጄ ወዳጄ ሆይ፤ በመንበርህ ዙሪያ በሚቆሙ እልፍ፤ አእላፋት ትጉሃን ዘንድ መላእክት ቃል ኪዳን ትገባልኝ ዘንድ እማልድሃለሁ። ልጄ ወዳጄ ሆይ፤ በሰማይና በምድር ስፋታቸው በደመናም ውስጥ በሚመላለሱ ረቂቃን መላእክት ቃል ኪዳን ትገባልኝ ዘንድ እማልድሃለሁ። ልጄ ወዳጄ ሆይ፤ ተራሮችና ኮረብቶች ከመፈጠራቸው አስቀድሞ በፀሐይና በጨረቃ ውስጥ በሚመላለሱ ብርሃናውያን መላእክት ቃል ኪዳን ትገባልኝ ዘንድ እማልድሃለሁ። በሬም ላምም ቢሆን ቢታመም ይህችን ጸሎት ቢደግሙላቸው ክፉ በሽታ አይነካቸውም፤ ይህችን መጽሐፍ በንጽሕና ለሚይዛት ሁሉ ከደዌው አድነዋለሁ። ከሚያስጨንቅ ችግርም እሠውረዋለሁ፤ ደዌውም ለሕይወትና ለጤናም ቢሆን እኔ ፈጥኜ አነሳዋለሁ። ኃጢአትም ቢኖርበት ይሠረይለታል። ደዌው ለሞት የታዘዘ ቢሆን እኔ አስቀድሜ መላእክተ ብርሃንን እልካለሁ፤ ነፍሱንም በክብር ተቀብለው ወደ እኔ ያመጧታል። መንፈሳውያን የሠራዊተ መላእክት አለቆችም በአዩት ጊዜ ደስ ይላቸዋል፤ ይህን ጸሎት በንጽሕና እየጸለየ የያዛትን ሰው በክንፋቸው እያጨበጨቡ በእግራቸው እያሸበሸቡ ይቀበሉታል በቅዱስ ወንጌል የተነገረውን አልሰማሽምን መቶ በጐች ያሉት ሰው ከመቶው አንዲቷ ብትጠፋበት ዘጠና ዘጠኙን በዱር ትቶ የጠፋችውን በግ ሊፈልግ እንዲሄድ፤ በአገኛትም ጊዜ በትከሻው ተሸክሞ ካልጠፉት ከዘጠና ዘጠኙ በጐች ይልቅ ጠፍታ በተገኘችው በግ ደስ እንደሚለው ባልንጀሮቹንና ጐረቤቶቹንም ጠርቶ የጠፋችው በጌ ተገኝታለችና ደስ ይበላችሁ ይላቸዋል። እውነት እውነት እላችኋለሁ ንስሓን ከማይሹ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ አንድ ኃጥእ ሰው በሰማይ ታላቅ ደስታ እንደሚደረግ፤ ሁለተኛም ይህችን መጽሐፍ የሚደግማትና የሚይዛት ሰው ሰማያውያን የመላእክት ሠራዊት ደስ ይሰኛሉ፤ ከዚህ ከሚያልፈው ዓለም ወደማይልፈው ዓለም ነፍሱ ከሥጋው ተለይታ በምትወጣበት ሰዓት ደብረ መቅደሴን አወርሰዋለሁ፤ ከባሕርይ አባቴ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቴ ከመንፈስ ቅዱስም ዘንድ አቀርበዋለሁ። ይህች መጽሐፍ ካለችበት ቦታ ይቅርታ ቸርነት ምሕረት ጥጋብ ተድላ ደስታ እስከ ዘለዓለም ድረስ ይሆናል በእውነት። ይህች ጸሎት በተደገመችበትና በተነበበችበት ቦታ ንዳድ እንቅጥቅጥ በያይነቱበሽታ ሁሉ አይቀርቡም። ይህችን የጸሎት መጽሐፍ በንጹሕ ለያዛት እሱን ልጆቹን ገንዘቡን ሀብቱን እባርካለሁ፤ በዚህ መጽሐፍ አምኖ በንጽሕ ልቡና በቅን ሃይማኖት ያለጥርጥር በማየ ጸሎቱ የተጠመቀ የጠጣ መንገዱን የጠረገ በቤቱ መድረክ ላይ የረጨ እኔ ጸሎቱን እሰማዋለሁ፤ እንድ ልቡም ፈቃድ አደርግለታለሁ፤ ሚካኤልና ገብርኤልም ፈቃዱን ይፈጽሙለት ዘንድ ዘወትር ወደ እሱ ይመጣሉ፤ ይህችን መጽሐፍ በንጽሕና የያዘው ሰው የሠራዊተ መላእክት አለቆች ዘወትር እየመጡ ይጐበኙታል እናቴ ማርያም ሆይ በሰማይና በምድር ይህን ሁሉ ዓሥራት (ተስፋ) ሰጠሁሽ፤ ቡርክት መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለባት እመቤታችንም ልጄ ወዳጄ ይህ የምትለኝ ሁሉ እውነት ነውን አለችው። ጌታም መልሶ እናቴ ማርያም ሆይ በእግዚአብሔር አባቴ በክርስቶስ ስሜ በእውነት በመንፈስ በጰራቅሊጦስ እውነት እንደሆነ ቃል ኪዳን ገባሁልሽ አላት። መልአከ ምክሬ በሆነው በሚካኤል የመወለዴን ዜና በአበሠረ በገብርኤል ቃል ኪዳን ገባሁልሽ። ክንፋቸው ስድስት በሆነ ምሉዓነ አዕይንት በሆኑ መንበሬን በሚሸከሙ ዐራቱ እንስሳት (ኩሩቤል) ቃል ኪዳን ገባሁልሽ፤ አነዋወሬን በአንድነት ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ እያመሰገኑ መንበሬን በሚያጥኑ በሃያዓራቱ ካህናተ ሰማይ ቃል ኪዳን ገባሁልሽ እልፍ ሆነው በቀኝ በሚቆሙ እልፍ ሆነው በግራ በሚቆሙ እልፍ ሆነው በበኋላ በሚቆሙ እልፍ ሆነው በፊቴ በሚቆሙ መላእክት ቃል ኪዳን ገባሁልሽ። በእልፍ አዕላፍት ብዙ የብዙ ብዙ በሚሆኑ ትጉሃን መላእክት ቃል ኪዳን ገባሁልሽ። የፍጥረት ተቀዳሚ በሆነ በአዳም በልጆቹም በአቤልና በሴት በቃይናን በመላኤል ቃል ኪዳን ገባሁልሽ። ዳግመኛ ምድርን በንፍር ውሃ እንዳላጠፋት ኪዳነ ሰማይ ወምድር በሰጠሁት በባሪያዬ በኖህ ቃል ኪዳን ገባሁልሽ። የትእዛዜ ጠባቂ ተቀዳሚ በኵር በሆነ በሴም ምሳሌየ በሆነ በመልከ ጼዴቅ ካህን፤ ቃል ኪዳን ገባሁልሽ። ስለወዳጄ ስለአብርሃም ስለባለሟሌ ስለ ይስሐቅ ዘሩን በዓሥራ ሁለት ነገድ ከፍዬ ስለአከበርኩት ስለያዕቆብም ቃል ኪዳን ገባሁልሽ። በይሁዳና በፋሬስ በዮሴፍና ብንያም በሌዊና ይሳኰር በዓሥራሁለቱ ነገደ እሥራኤል ቍጥር ቃል ኪዳን ገባሁልሽ። ንጹሓን ቅዱሳን በሚሆኑ በቀደሙ አባቶች ቃል ኪዳን ገባሁልሽ። ጸሐፍተ ትእዛዝ በሆኑ በሄኖክና በኤልያስ ቃል ኪዳን ገባሁልሽ። ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በተቀመጥኩባት ንጽሕት በሆነች ማኅፀንሽ ቃል ኪዳን ገባሁልሽ። ጣፋጭነቱ ከመዓር ከስኳር ይልቅ የሚጥመው ንጹሕነቱ ከኤዶም ምንጭ ውሀ፤ ንጣቱ ከበረዶና ከወተት የበለጠውን ወተት መግበው ባሳደጉኝ ጡቶችሽ ቃል ኪዳን ገባሁልሽ። ትእዛዜንና ሕጌን ባስተማሩ ዓሥራ አምቱ ነቢያት ሄሮድስ ባስገደላቸው ዓሥራ ዐራት እልፍ የቤተ ልሔም ሕፃናት ቃል ኪዳን ገባሁልሽ። የወንጌልና መንግሥት ለዓለም በሰበኩ ሐዋርያት ስለእኔ ሲሉ ነፍሳቸውን ለሞት አሳልፈው ስለሰጡ ሰባሁለቱ አርድእት ቃል ኪዳን ገባሁልሽ። ዙፋኔ በተዘጋጀባት ሉዓላዊት ሰማይ የእግሬ መረገጫ በሆነችው ታሕታዊት ምድር ቃል ኪዳን ገባሁልሽ። ነደ እሳት በሆነ በአርያም ሰማይ ቃል ኪዳን ገባሁልሽ። በተሰቀልኩበት ዕፀ መስቀል እጅና እግሬ በተቸነከረበት ቀኖት (ችንካር) በጦር በተወጋው ጐኔ ቃል ኪዳን ገባሁልሽ። በዕለተ ዓርብ በፈሰሰው ደሜ በሕማሜና፤ በሞቴ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊትም በከርሠ መቃብር ባደርኩበት ቃል ኪዳን ገባሁልሽ። ከመቃብር ወጥቼ አዳምን ከነልጆቹ ከሲኦል ለማውጣት ወደሲኦል በመውረዴ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቼ ሙስና መቃብርን አጥፍቼ በመነሣቴ በዐርባኛው ቀን ወደሰማይ በማረጌ ዳግመኛም ዓለምን ለማሳለፍ በታላቅ ምስጋና በምመጣበት ቃል ኪዳን ገባሁልሽ። ክቡር በሆነ፤ ደሜ ቅዱስ በሆነ ሥጋዬም ቃል ኪዳን ገባሁልሽ። የሙሽራ አምሳል በሆነች በቅድስት ቤተ ክርስቲያን-ከዕለታት መርጬ የተወለድኩባት፤ የተጠመቅሁባት፤ ለሰው ልጅ ደኅንነትን የምታስገኝ ትንሣኤዬንም የገለጡባት በሰንበተ ክርስቲያን ቃል ኪዳን ገባሁልሽ። በደብረ ዘይት በተቀደሰውም በጸዮን ደብረ መንግሥቴ፤ በመቃብሬ ቦታ በጎልጎታ፤ ንጹሕ ብሩህ በሆነ ደም ግባትሽ፤ ንጹሓት ክቡራት በሆኑ ልብሶችሽ በነዚህ ሁሉ ቃል ኪዳን ገባሁልሽ። እናቴ ድንግል ማርያም ሆይ! የሰጠሁሽን ቃል ኪዳን እንዳልነሳሽ አማንየ ብዬ በራሴ ማልሁልሽ በአንቺ ስምም በሚቀደስበት ታቦት እኔ እረባለሁ። መሥዋዕቱንም አሻትታለሁ። እንደ አቤልም መሥዋዕት እቀበለዋለሁ። መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለባት እመቤታችንም መለሰችለት። አንተ ብሩክ ነህ። ሰማያዊ አባትህም ቡሩክ ነው። የባሕርይ ሕይወትህ መንፈስ ቅዱስም የተባረከ ነው አለች። ይህን ሁሉ በቸርነትህ ስለሰጠኸኝ አቤቱ ለአንተ ምስጋና ይገባል፤ ለቸር አባትህም ምስጋና ይገባል፤ ማኅየዊ ለሚሆን ለመንፈስ ቅዱስም ምስጋና፤ ይገባል። ዛሬም ለዘወትርም እስከ ዘላለሙ አሜን። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለእናቱ ይህን ነግሯት ከፈጸመ በኋላ ሰላምት ሰጥቷት በታላቅ ምስጋና ወደ ሰማይ ዐረገ። እሷም እግዚአብሔርን እያመሰገነች ወደ ቤቷ ተመለሰች። እንዲህ እያለች፤ አቤቱ አንተ የተመሰገንህ ነህ፤ ስምህም የተመሰገነ ነው፤ የመንግሥትህም ስም ይባረክ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ክብር ዕንዕ፤ ለአንተ ይገባል፤ ዛሬም ዘወትርም እስከ ዘላለሙ ድረስ አሜን። እመቤቴ ማርያም ሆይ! በዚህ ቃል ኪዳንሽ ከተንኮለኞች ሰዎች እጅ ከጸዋጋን አጋንንትም መከራ እኔን አገልጋይህን_____________አድኝኝ አሜን። ከሦስተኛው ሰማይም በደረሰ ጊዜ መናፍስት ርኵሳን አይቃወሙትም ፤ ፀዋጋን አጋንንት ከሱ ጋር አይቆሙም፤ ሊቀርቡትም አይችሉም ዳግመኛም እኔ በዚያ አስፈሪ በሆነ ሰዓት እረዳት እሆነዋለሁ። እኔና የባሕርይ አባቴ አብ የባሕርይ ሕይወቴ የዕውነት መንፈስ ጰራቅሊጦስ ወደ እሱ እንመጣለን አስራሁለቱ ሊቃነ መላእክትም ከዝርግፍ ወርቅ ጋር የወርቅ ጥናቸውን ይዘው የመጣሉ፤ ቀስተ ደመና በመሰለ በናርዶስ ሽቱ መብረቅም በመሰለ የእሳት ሠረገላ ሁነን ይህችን ጸሎት የያዘ ስው እንቀበለው ዘንድ እስከ አምስተኛው ሰማይ ድረስ እንወርዳለን፤ በደረቴ አቅፌ ባሕረ እሳትን አሻግረዋለሁ፤ ወደ መንበረ መንግሥቴም አቀርበዋለሁ። |