colormap #003366#336699#3366CC#003399#000099#0000CC#000066#006666#006699#0099CC#0066CC#0033CC#0000FF#3333FF#333399#669999#009999#33CCCC#00CCFF#0099FF#0066FF#3366FF#3333CC#666699#339966#00CC99#00FFCC#00FFFF#33CCFF#3399FF#6699FF#6666FF#6600FF#6600CC#339933#00CC66#00FF99#66FFCC#66FFFF#66CCFF#99CCFF#9999FF#9966FF#9933FF#9900FF#006600#00CC00#00FF00#66FF99#99FFCC#CCFFFF#CCCCFF#CC99FF#CC66FF#CC33FF#CC00FF#9900CC#003300#009933#33CC33#66FF66#99FF99#CCFFCC#FFFFFF#FFCCFF#FF99FF#FF66FF#FF00FF#CC00CC#660066#336600#009900#66FF33#99FF66#CCFF99#FFFFCC#FFCCCC#FF99CC#FF66CC#FF33CC#CC0099#993399#333300#669900#99FF33#CCFF66#FFFF99#FFCC99#FF9999#FF6699#FF3399#CC3399#990099#666633#99CC00#CCFF33#FFFF66#FFCC66#FF9966#FF6666#FF0066#CC6699#993366#999966#CCCC00#FFFF00#FFCC00#FF9933#FF6600#FF5050#CC0066#660033#996633#CC9900#FF9900#CC6600#FF3300#FF0000#CC0000#990033#663300#996600#CC3300#993300#990000#800000#993333

ውዳሴ አምላክ ዘዘወትር

ከቁጣ የራቅህ ይቅርታህ የበዛ ጻድቅ ልበ ሰፊ መሐሪ ሆይ አከብርሃለሁ። ዕለት ዕለት ስበድል ታግሠህ ጠብቀኸኛልና፤ ንስሐ እንገባ ዘንድም ለሁላችን ሥልጣን ሰጠኸን፤ስለዚህ እናከብርህ ዘንድ ክቡር ስምህን እናመሰግን ዘንድ ታገስኸን ስለምትሠራው ሁሉ የፍጥረት ሹም ሆይ ኀዘንና ፍርሃትን ድካምንም የምታመጣበት ጊዜ አለና። በነቢያት የዘለፍክበት ጊዜም ነበርና ኋላ ግን በአንድ ልጅህ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መታየት ጐበኘኸን። ካለመኖር ወደ መኖር የፈጠርኸን አንተ ነህ አባታችንም ጌታችንም አንተ ነህ። ችጋረኛ የምሆን እኔስ ከፊትህ ልናገር አይገባኝም ከኃጥአን የምበልጥ ኃጥእ ነኝና። ክብርት ሕግህንም ያረከስኩ ነኝና ከኃጢአቴ ትዕግሥትህን ስለ አበዛህልኝ አመስግንሃለሁ። በፈቃድህ ቸል ብለህ እስከ አሁን ያለ ፍርድ ጠበቅኸኝ። እኔ ግን ስለ በደሌ ለፍርድ የተገባሁ ነኝ ስለ ኃጢአቴም ለስቃይና ከፊትህ ለመውደቅ፤ ነገር ግን ሰውን ስለመውደድህና ስለ ትዕግሥትህ እስከ አሁን ጠበቅኸኝ። መሐሪ ጌታ ሆይ፤ ስለዚህ አመሰግንሃለሁ መጠን ለሌላት ትዕግሥትህና ለጌትነትህ የሚገባ ምስጋናን አመሰግንህ ዘንድ ሥልጣን የሌለኝ የተናቅሁ ጎስቋላም ብሆን የእኔን የባሪያህን ጎስቋላና ደካማ ልመናዬን ስማኝ። ወሰን በሌላት በፍቅርህ ብዛት እስከ ዘለዓለሙ ክብርና ምስጋና መገዛትም ለአንተ ይገባል አሜን በእውነት። ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ ዕቀብ ሕይወትየ ወሥረይ ኃጢአትየ ሊተ ለ....።

ማር ይስሐቅ ፪ኛ ምዕራፍ

ወንድሜ ሰውነትህን ዘወትር ዝለፋት ከሥጋ የምትለዪበት የምታልፊበት ጊዜ ደርሷል በላት። ባለሽበት ኋላ ጥለሽው በምትሄጂ ሥራ ዛሬ ለምን ደስ ይልሻል? እርሱን በማየት ጥቂት ዘመን ተድላ ደስታ የምታደርጊበት ኋላ ብዙ ዘመን በምታጭው የቀደመ ሥራሽን እወቂ የሠራሽው ሥራ ምንም እንደሆነ አስቢ፤ጽድቅም እንደሆነ ኃጢአትም እንደሆነ፤ ያለ ዘመንሽን ከማን ጋር ፈጸምሽው? ከጌታ ጋር ነው? ወይስ ከሰይጣን ጋር ነው? ደክመሽ የሠራሽውን የሚቀበልሽ ማን ነው? ጌታ ነው? ወይስ ሰይጣን ነው? በትሩፋትሽ ማንን ደስ አሰኘሽ? ጌታን ነው ወይስ ሰይጣንን ነው? በጊዜ ሞትሽ ሊዋሐድሽ የሚመጣው ማን ነው? በመንግሥተ ሰማይ ዐርፈሽ ትኖሪ ዘንድ በሥራሽ ደስ ያለው ማን ነው? ለማን ብለሽ ደከምሽ? ለማን ብለሽ መከራ ተቀበልሽ? ለመንግሥተ ሰማይ ብለሽ ነውን? ደስ ብሎሽ ታገኚው ዘንድ አኳኋኑስ ምንድነው? ነፍስሽ ከሥጋሽ በተለየች ጊዜ በመንግሥተ ሰማይ ይዋሐድሽ ዘንድ ገንዘብ ያደረግሽው ምንድነው ምን ምግባር ነው? በማናቸው እርሻ ሊያውሉሽ ተቃጠሩሽ በማናቸውስ መዓርግ ተቃጠሩሽ? በባለሠላሳ ነው? በባለስልሳ ነው? ወይስ በባለመቶ ነው? ነፍስሽ ከሥጋሽ በምትለይበት ፀሐይ ዕድሜሽ በገባ ጊዜ ዋጋሽን እሰጥሻለሁ ያለሽ ማነው? ጌታ ነው? ወይስ ዲያብሎስ ነው? ነፍሴ ሆይ ሰውነትሽን መርምሪ ዕዳሽ በማናቸው ቦታ እንደሆነ እወቂ፤ መንግሥተ ሰማይም እንደሆነ ገሃነምም እነደሆነ እወቂ ለሚያርሱ ሰዎች አሞጭ እሬት የሚያፈራ እርሻሽን ያረስሽ ብትሆኝ ማለት በሚሠሩት ሰዎች ፍዳን የሚያመጣ ኃጢአትን ብትሠሪ እያዘንሽ እየተቆረቆርሽ አልቅሽ ለምኝ። ከቍርባን ከመሥዋዕት ይልቅ በሱ ምክንያት ወዶ በሰው በሚያድርበት ገንዘብ ያድርበት ዘንድ ክቡራን መላእክት ደስ በሚላቸው ደስ ይላቸው ዘንድ አንደበትሽ እየራራ ያመስግን። ግራ ቀኝ ፊትሽን በዕንባ እጠቢው መንፈስ ቅዱስ ያድርብሽ ዘንድ ከኃጢአትሽ ይለይሽ ያነጻሽ ዘንድ መጥቶ ያድርብሽ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እያለቀስሽ ለምኚልኝ የልቅሶ ዜማ ማርያምን ማርታን ጥሪያቸው ማለት አብነት አድሪጊያቸው የልቅሶ ባለቤቶች ናቸውና። ለአልዓዛር ብሎ ወደ አለቀሰ ወደ ጌታ ያዝንልሽ ዘንድ ለምኝ ራርቶ ብዙ ልቅሶን ወደሚሰጥ ጌታ ለምኝ። ምርር ብዬ ያለቀስሁት ዕንባዬን ተቀበልልኝ እያልሽ ወደ እርሱ አልቅሽ። በመልዕልተ መስቀል በተቀበልከው መከራ ከደዌ ኃጢአት አድነኝ። በመስቀል ላይ በቆሰልከው ቍስል ከቍስለ ኃጢአቴ አድነኝ ከመከራ አድነኝ። ደሜን በደምህ አንጻው ብለሽ ለምኝ። ከፍዳ ከኃጢአት የሚያድን ደምህን ከሥጋዬ ጋር አዋሕድልኝ። በመስቀል ላይ በጠጣኸው ሐሞት፤ ሰይጣን እሷን ከሚያሠራት ኃጢአት ለይተህ በሰውነቴ ጣዕም አሳድርባት። በመስቀል ላይ የተዘረጋ ሥጋህ፤ አጋንንት በምክራቸው ወደ ገሃነም ለማውረድ የሳቡት ልቡናዬን ወደ አንተ ይስቀለው ወደ ፈያታይ ዘየማን ዘንበል ባለ እራስህ አጋንንት በብረት ኃጢአት የመቱት ራሴን ከፍ ከፍ አድርገው። «እምከመ ተለዓልኩ እምድር እስሕብ ኵሎ ኀቤየ» ብለህ በማይታበል ቃልህ እንደተናገርክ። ዮሐ.፲፪፥፴፪ በመስቀል የተቸነከሩ እጆችህ ከኃጢአት ከፍ ከፍ ያድርጉኝ ርኩሳን አይሁድ ትፍ ያሉበት የጸፉት ፊትህ ኃጢአት ሠርቶ ያደፈ ሰውነቴን ፊቴን ይጠበው። በመስቀል ተሰቅለህ ሳለህ «አባ አመኃፅን ነፍስየ ውስተ እዴከ» ሉቃ.፳፫፥፵፮ ብለህ የለየሃት ነፍስህ በቸርነትህ መርታ አንተ ወደ አለህበት ታድርሰኝ። «ምነው አታዝንም?» ትለኝ እንደሆነ አንተን ለመሻት ያዘነ ልቡና የለኝምና። «ምነው ንስሓ አትገባም?» ትለኝ እንደሆነ፤ ጻድቃን ወደ ማታልፍ ርስታቸው ወደ መንግሥተ ሰማያት ተመርተው የሚደርሱበት ንስሓ ኀዘን የለኝም፤ እሊያ ንስሓ ገብተው የሠሩትን ሥራ አልሠራሁምና። ጌታዬ ሆይ ኃጢአትን የሚያስተሠርይ እንባ የለኝም የዚህን ዓለም ሥራ በማሰብ ልቦናዬ ደከመ፤ተቆርቁሮ ወደ አንተ ያለቅስ ዘንድ አይቻለውም እነሆ በኃጢአት ብዛት ልቡናዬ ተባረደ። አንተን ወዶ በሚያፈሰው እንባ ፍቅር መቃጠል አይቻለውም። የሀብታት የምስጢራት መገኛ ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ አንተ ግን ራርተህ ፈጽሞ መመለስን ስጠኝ። በፍጹም ልቡናዬ አንተን ለመሻት እወጣ ዘንድ ያዘነ ልቡናን ስጠኝ። ከአንተ በመራቅ ከአንተ በመለየት ተሰጥቶኝ የነበረውን ክብር አጣዋለሁ። ቸር ንጉሥ ሆይ ዛሬ ግን በለጋስነትህ ስጠኝ።

ዘመን የሌለው ልደትን አካልን ዘእምአካል፣ባሕርይን ዘእምባሕርይ የወለደ አባትህ አንተን መምሰልን ያጸናብኝ፤ ያሳድርብኝ ዘንድ ከክብርህ ወገን ስጠኝ ካልኩህ አንተ ግን አትጣለኝ። ከከበረ ሕግህ ወጣሁ ከፊትህ ተለየሁ። አንተም እኔን ለመፈለግ ውጣ። «እንደገባ ይውጣ እንደወጣ ይቅር» አትበለኝ። ምእመናን ወደ አሉበት ወደ መንግሥተ ሰማይ አግባኝ። ከመንጋ በጎች ከተመረጡ ከጻድቃን ጋር እንድቆጠር አድርገኝ። ንጹሕ ልቡናን ላግኛት የሚል ንጹሕ ልብ የሚረዳት የአምላክነትህ ገንዘብ የምትሆን እህል ምስጢርህን መግበኝ ከአንተ የተገኘውን ምስጢር የማይበት በአንተ ስለአመኑ ስለሚጨነቁ የሚሰጥ ጸጋ ክብር ነው የጭንቅ ጭንቅ የሚሆን መከራውን ለሚታገሡ ልዩ ልዩ የሚሆን ሥቃይን ለሚታገሡ ሰዎች የሚሰጥ ክብር ለሁላችን ምስጢር የሚገለጽበት ክብሩን በቅተን እናገኘው ዘንድ ጸጋውን የበቃን ሆነን ያገኘን ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነት ሰውን በመውደዱ ዛሬ በአለው ዓለም በሚመጣውም ዓለም፤በማይፈጸመው ዓለም ሰውን በመውደዱ አሜን በእውነት። ኦ እግዚእየ ወአምላኪየ ኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረት መገኛ መዓትህ የራቀ ትዕግሥትህ የቀረበ ቸርነትህ የበዛ ዕቀብ ሕይወትየ ወሥረይ ኃጢአትየ ሊተ ለ.......።

ጸሎተ ምናሴ ፩፥፩-፲፫

አቤቱ ዓለምን ሁሉ የምትገዛ የአባቶቻችን አምላካቸው። የአብርሃምና የይስሐቅ የያዕቆብም የጻድቃን የዘራቸውም ሁሉ። ሰማይና ምድርን ከዓለሞቻቸውም ሁሉ ጋር የሠራህ። ባሕርን በቃልህ ትእዛዝ የገሠጽሃት፤ጥልቆችን የዘረጋህ የሚያስፈራውንም ያተምህ ይኸውም በምስጉን ስምህ ነው። ሁሉ ከኃይልህ ፊት የሚናወጽና የሚንቀጠቀጥ ሆይ ለምስጋናህ ከፍታ ዳርቻ የለውምና የቍጣህ መቅሠፍት በኃጥአን ላይ የሚያስፈራ ነው። ለትእዛዝህ ይቅርታ ስፍር ቍጥር የለውም፤ እግዚአብሔር ሆይ አንተ ብቻህን ከፍ ያልህ ነህና። ከቍጣ የራቅህ ይቅርታህም የበዛ መሓሪ ነህና። በሰው ልጆች በደል ላይም የምትመለስ ነህ። አሁንም የጻድቃን አምላክ ሆይ ንስሓን የሠራኸው ለጻድቅ አይደለምና አንተን ላልበደሉ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም አይደለምና፤ ወደ እኔ ወደ ኃጢአተኛው ንስሐ ተመለስ እንጂ። ከባሕር አሸዋ ቁጥር ይልቅ በድያለሁና። ኃጢአቴም ብዙ ነውና፤ ከበደሌም ብዛት የተነሣ የሰማይን ከፍታ አይ ዘንድ ላንጋጥጥ አግባቤ አይደለም። በእግር ብረት ደከምኩ ነፍሴን ከኃጢአቴ አሳርፋት ዘንድ በዚሁም አላረፍሁም፤ ቍጣህን አነሣሥቻለሁና፤ ክፉውንም በፊትህ ሠርቻለሁና ክፉውንም ስጠብቅ የማይረባኝንም ሳበዛ። አሁንም በልቡናዬ ጉልበት እሰግዳለሁ፤ የአንተን ምህረት እየለመንኩ አቤቱ ጌታዬን በደልኩ ኃጢአቴንም እታመናለሁ። እማለላለሁ እለምንህማለሁ። ይቅር በለኝ አቤቱ ይቅር በለኝ። ለኃጢአቴም አሳልፈህ አትስጠኝ። ለዘላለምም ክፋቴን አትጠባበቀኝ፤በምድርም ጥልቅ ውስጥ አትበቀለኝ፤ አቤቱ አንተ ንስሐ የሚገቡ ሰዎች አምላክ ሆይ፤ ቸርነትህ በእኔ ላይ ይገለጽ ዘንድ አግባቤ ሳይሆን በቸርነትህ ብዛት አዳንከኝ። በሕይወቴ ዘመን ሁሉና በጊዜው ሁሉ አመሰግንሃለሁ። የሰማዮች ሠራዊት ሁሉ አንተን ያመሰግናሉ። ለዘላለምም ምስጋና ለአንተ ይገባል አሜን በእውነት።

ውዳሴ አምላክ ዘ እሑድ
የንስሐ ሥርዓት

የመመኘቴ ጸሎት ጌታዬ መድሐኒቴ ኢየሱስ ሆይ እንግዲህ በእኒህ ሁሉ አማላጅነት ወደእኔ ና አትዘግይብኝ ነፍሴ እና ልቤ ኢየሱስ ክርስቶስን ፈጥነህ ና በሉት አፌ ኢየሱስ ክርስቶስን ና በለው የጻድቅነት ጸሐይ ሆይ የነፍሴን ጨለማ አርቅልኝ ሰማያዊ እሳት ሆይ በዓለማዊ ፍቅር ብርድ ለታሰረብኝ ልቤ ያንተን ፍቅር ሙቀት ስጥልኝ ጌታዬ ሆይ በወንጌል ለመቶ አለቃ ወደ ቤትህ እመጣለሁ ልጅህንም እፈውስልሀለሁ እንዳልከው ለነፍሴ ወዳንቺ እመጣለሁ እፈውስሻለሁ በልልኝ ከእንግዲህ ወዲህ ክፉ እንዳልናገር አፌን ፈውስኝ ክፉ እንዳለይ አይኔን ፈውስልኝ ክፉ እንዳይሰሩ ነፍሴንና ስጋዬን ፈውስልኝ ጌታዬ ሆይ የእኔን የሎሌህን ክፋት ልትተው ና አትዘግይብኝ ቅዱስ መልአኬ ነፍሴን እጅግ የምትወድ ጠባቂዬ ሆይ ስለ እግዚአብሔር ምስጋናና ክብር ይህንን ኑዛዜ በቀኖና በትህትና በሐዘን በፍቅር እንዳደርገው አግዘኝ ስለኑዛዜ ምክር እንዲህ እያለ የሀዘን ጸሎት እያደረገ በትህትና በልብ ይጸጸት

አቤቱ የጠራ የልቦናን ለቅሶ ስጠኝ ጌታዬ ሆይ በእኔ የጸኑ እሾህ እና አሜኬላን ክዳት ተንኮልንም አጥፋልኝ ዘወትር የሚያቃጥል ልቅሶን ስጠኝ አቤቱ የሰይጣን ገንዘብ የሚሆን የኃጢአትን ጣዕም ስር ከእኔ ነቅሎ የሚጥል ልቅሶን ስጠኝ፡፡ አቤቱ ከኃጢአት የሚመለሱ ሰዎችን ልቅሶ ስጠኝ አቤቱ የቅዱሳንን ልቅሶ ስጠኝ፡፡ አቤቱ በኃጢአት ሳለ እንዳይሞት ስለራሱ ያለቀሰ የዳዊትን ዕንባ ስጠኝ ፡፡

ጌታዬ ሆይ እንደኔ የበደለ የለምና እኔም እንደወደቅሁት አወዳደቅ የወደቀ የለምና እኔ እንደተፈተንኩት የተፈተነ የለምና፡፡ የሠራኋትም ኃጢአት አንዲት ብቻ አይደለችምና በኃጢአቴ የሌላውን ጽድቅ አጠፋሁ እንጂ፡፡

ጌታዬ ሆይ እኔን ሳላውቅ የፈጠርኸኝ አንተ ነህ ፡፡አንተ ጌታዬ የከበርህ መምህር ኃያል ገናና ነህ እኔ ባርያህ ግን የተናቅሁ ጎስቋላ ደካማ ነኝ አፌ የሚሸት ነው አንደበቴም ዲዳ ነው፡፡ እኔም ኃጥእ ነኝ፡፡ ደካማ ነኝ ልቤም የረከሰ ነው፡፡ በቸርነትህ ተጠግቼ እጠራሀለሁ የጻድቁንና የኃጥኡን ጸሎት የክፉውን የምትሰማ አንተ ነህና ያለ አንተም ቸር የለምና እንደ አንተ ያለ ይቅር ባይ የለምና፡፡

ጌታዬ ሆይ የነጻች የእጅህ ሥራ ነኝና ስለ ኃጢአቴ ቸል አትበለገኝ አቤቱ ሥጋዬን አንጻው ሕፀፄን አውቄ ከመጠኔ እንዳልወጣ አቤቱ ጠላት ድል እንዳይነሳኝ ኃይልን ስጠኝ በክብርት ጥምቀትህ የተሠራች ቤት ሥጋዬን እንዳያፈርሳት በከፋች ኃጢአት እንዳያሳድፋኝ ስለ ኃጢአቴ ሥርየት ወደ አንተ እማፀናለሁ፡፡ አቤቱ ነፍሴ እንዳትጎዳ አደራህን ፡፡

ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ስለ ጉስቊልናዬና ስለ ጉዳቴ እማፀናለሁ ስለ ኃዘኔና ስለ መከራዬ በአንተ እማፀናለሁ ስለ መልኬ ጥፋትና ስለበደሌም በአንተ እማፀናለሁ፡፡ ብሩህ ሁኜ ሁሉን እንዳላይ የጠቆርሁ ኃጥእ ነኝና ላልተመለሱ ፍርድህንና ሞትን ማሰብ ስጠኝ አቤቱ በደሌንና ነውሬን የሚያጥብ ዕንባን ስጠኝ አቤቱ፡፡አቤቱ አንተን የሚያገለግል ዕንባን ስጠኝ አቤቱ ልዩ እንባን ስጠኝ፡፡ አቤቱ ቀጡ ዕንባን ስጠኝ፡፡አቤቱ ኀዘኔን የሚያርቅልኝንና የፊቴን ጥቁረት የሚያርቅልኝ እንባን ስጠኝ፡፡ አቤቱ ከዓይኔ ፈሶ የአካሌን እድፍ የሚያጥብልኝ ዕንባን ስጠኝ፡፡ አቤቱ አንተን ደስ የሚያሰኝ ደስ ብሎህ የምትቀበለው ዕንባን ስጠኝ፡፡

የተነሳሕያንን ዕንባን የምትቀበል ሆይ ወንድማቸውን ከመቃብር እስክታነሣላቸው ድረስ ሳያቋርጡ እንዳፈሰሱት እንደ አልአዛር እህቶች ያለ ዕንባን ስጠኝ ፡፡አንተ የተቀበልከው ጽኑ ልቅሶን እንደ አለቀሰ እንደ ጴጥሮስ ያለ ዕንባን ስጠኝ ፡፡

ከንጹሐን እግሮችህ ላይ ዕንባዋን አፍስሳ በራሷ ፀጉር እንደ አደፈችው እንደ ሴሰኛዪቱ ሴት ያለ ልቅሶን ስጠኝ፡፡ልቅሶዋም ስለ ንስሐዋና ስለ ሕይወትዋ ሆነ፡፡

ልጅዋን እንዳነሣህላት እንደ ጎስቋላይቱ ድኻ ልቅሶ ያለ ዕንባን ስጠኝ ፡፡አልጋዬን በዕንባዬ አርሰዋለሁ ምንጣፌን በዕንባዬ አጥበዋለሁ ብሎ በስድስተኛው መዝሙር እንደ ተናገራት እንደ ዳዊት ያለ ዕንባን ስጠኝ ፡፡

አቤቱ እንደ አባቶቼ መምህራን ያለ ዕንባን ስጠኝ፡፡ እንደ ተነሳሕያን ኃጥአን ያለ ዕንባን ስጠኝ አቤቱ እንደ ባሕር በምትፈስ ዕንባ እጠበኝ፡፡ አቤቱ ጌታ ሆይ የተዘጋ ደጅህን ክፈትልኝ፡፡ ጌታዬ ሆይ የማያቋርጥ የዕንባን ምንጭ ክፈትልኝ፡፡ አቤቱ የማያቋርጡ የዕንባዎች ጎርፍን አፍስልኝ ፡፡ስለበደሌና ስለኃጢአቴ ብዛት ስለ ነፍሴም ጉዳት የንግድ ገንዘብ ስለሚሆን ስለራሴም ጥፋት አቤቱ ይቅር በለኝ፡፡

ጌታዬ ሆይ ነፍሴን ከሥጋዬ እስክትለይ ርዳት የተበላሸች የወይን ቦታ ስለ መልካም ፍሬ ፈንታም ርኩስ ፈቃዴና ኃጢአቴ የሰለጠኑበትን አርማት ኮትኩታት፡፡

ጌታዬ ሆይ ወደ መመቸቴ ፈቃድ አታግባኝ፡፡ ፍርድህንም ፈርቼ ነፍሴን ከፊትህ ጥያታለሁ፡፡ አቤቱ ከይቅርታህ ለምመጸወት ድኻ እዘንልኝ ከርኅራኄህ ትሩፋት የምለምን ችግረኛህንም አታሳፍረኝ፡፡ በበደሌና በኃጢአቴ መታደስ እኔ ወራዳ ድኻ ነኝና በከሃኒነትህ ከኃጢአት እድፍ አንጻኝ ስምህን ለሚወዱ ለባሮችህ ባዘጋጀኸው በንስሐ ዕንባ እጠበኝ ፡፡

አቤቱ ኃፍረቴንና ኃሣሬን ሠውራት፡፡ በፍጥረቱ በምትፈርድበት ጊዜ የናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ልመናዬን ስማኝ ፈጣሪዬ ሆይ ፊትህን ከልመናዬ አትመልስ፡፡ልቅሶዬን ተቀበል ዕንባዬንም አታሳፍር አኔ ጥገኛህ ነኝና ጌታዬ ሆይ ስለ ኃ ጢአቴ ብዛት እገዛልኻለሁ፡፡

ጌታዬ ሆይ እስከዘመኔ ፍጻሜ ከቡር ስምህን አመሰግናለሁ ኪሩቤል ሱራፌልም የመላእክትም ሠራዊት ሁሉ አንተን ያመሰግናሉ ለዘላለሙ አሜን በእውነት ይደረግልገኝ፡፡

መዝሙረ ዳዊት 120

1 ዓይኖቼ ወደ ተራሮች አነሣሁ ረዳቴ ከወዴት ይምጣ?
2 ረዳቴ ሰማይና ምድርን ከሠራ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።
3 እግርህን ለመናወጥ አይሰጠውም የሚጠብቅህም አይተኛም።
4 እነሆ፥ እስራኤልን የሚጠብቅ አይተኛም አያንቀላፋምም።
5 እግዚአብሔር ይጠብቅሃል፥ እግዚአብሔርም በቀኝ እጅህ በኩል ይጋርድሃል።
6 ፀሐይ በቀን አያቃጥልህም ጨረቃም በሌሊት።
7 እግዚአብሔር ከክፉ ሁሉ ይጠብቅሃል፥ ነፍስህንም ይጠብቃታል።
8 ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም እግዚአብሔር መውጣትህና መግባትህን ይጠብቃል።

ውዳሴ አምላክ ዘሰኑይ

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስቅዱስ ስም አምነን የቂሳርያ ኤጲስ ቆጶስ ባስልዮስ የደረሰውን የልመናና የምልጃ ጸሎት ያለበትን ዘወትር ሊጸልዩት የሚገባ ውዳሴ አምላክ የሚባል መጽሐፍ በእግዚአብሔር አጋዥነት እንጀምራለን የአባታችን የባስልዮስ ጸሎት ይጠብቀን ረድኤቱ አይለየን አሜን ይደረግን፡፡

አምላኬ ሆይ ሠውሬ የሠራሁትን ሁሉ ኃጢአት አንተ ታውቀዋለህ ኩላሊትንም ልቡናንም የምትመረምር አንተ ነህ ሠውሬ የሠራሁትን የሥራዬን ክፋት አንተ ታውቀዋለህ ክፉ ሥራዬን አይተህ በኔ ለመፍረድ የማትቸኩል ከተድላዬ የማታዋርደኝ አንተ ነህ በወደቅሁም ጊዜ አካሄዴን የማታዋርድ

አንተ ነህ በጎ አድራጊ ይቅር ባይ ሆይ አትቸኩልም አንተስ መመለሴንም እየጠበቅህ ትዕግስትህን አበዛህልኝ እኔም ከእንቅልፌ ነቅቼ ይቅርታህን ስፈልግ ወዳንተ ገሠገሥኩ ንስሐ የሚገባውን ሰው ንስሐውን እንድትቀበው አውቄ ባለኝታህ ጸንቼ ወዳንተ ገሠገሥኩ የተናቅሁ ድሀ እኔ እለምንሃለሁ ከወደቅሁበት ታነሣኝ ዘንድ ኃጢአቴንም ትተላለፋት ዘንድ ንስሐዬንም ትቀበለኝ ዘንድ ከመዓርጌ አዋርዶ ስለጣለኝ ጠላት እንዳይመካ ሳትነፍግ ሳትሳሳ የምትሰጥ በጎ አሳቢ ቸር ጌታችን ፈጣሪያችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ አንተ በታመነ ቃላህ በክቡር ወንጌልህ እሹ ታገኛላችሁ ለምኑ ይሰጣችኋል ደጅ ምቱ ይከፈትላችኋል ብለህ ተናግረሃል (ማቴ ፯፡፯)

አቤቱ ችጋረኛ ድሀ የምሆን እኔም እውነተኛ ነገርህን አለኝታ ተቀብዬ በቃለህ ጸንቼ ኃጢአቴን አምኜ እየማለድሁ እነሆ በፊትህ ቆሜ አለሁ፡፡

ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ አለኝታዬን ቆርጠህ እንዳታሳፍረኝ እለምንሃለሁ በደካማነቴ ራርተህ ኃጢአቴን ይቅር ትለኝ ዘንድ ፊትህንም ከኔ እናዳትመልስ ያን ጊዜ አንተን ለመለመን የማልበቃ ኃጥእ በደለኛ እሆናለሁ ያደፍኩ የረከስኩ ነኝና፡፡

ነገር ግን በይቅርታህና በቸርነትህ ብዛት የፍጥረትህን ዕርቅና መዳንን በመውደድህ ነገሬን መልስልኝ ልቅሶዬንም ተቀበለኝ ጌታዬ ፈጣሪዬ ሆይ የሥራዬን ክፋት የኃጢአቴን ብዛት አይተህ ዕንባዬን አታሳፍረኝ እንደ እውነተኛ አለኝታህ በክቡር ስምህ እንደማመኔ ይደረግልኝ እንጂ የነጻች የእጅህ ሥራ የምሆን እኔ ከባሮችህ ወገን ነኝና እኔም በክቡር ምሳሌህና በመልክህ ተፈጥሬ አለሁና በጥበብህ ከፈጠርኻቸው ከባሮችህ ወገን ስለሆንኩ ስለዚህ ደፍሬ የረከሰች አንደበቴን ገልጨ እለምንሃለሁ፡፡

ኃጢአቴን ይቅር ትለኝ ዘንድ ንስሐዬንም ትቀበለኝ ዘንድ ጽኑዕ ሥልጣን ከሃሊነት ያለህ ቸር ሆይ ጎስቋላ ድሀ የምሆን እኔን በይቅርታህ እንድታድነኝ በቸርነትህ ታደገኝ የበዛች ኃጢአቴንም በደሌንም አርቅልኝ እኔ የተከዝኩ በደለኛ ነኝና፡፡

አቤቱ በምለምንህ ጊዜ ፊትህን ከኔ ከባርያህ አትመልስ አቤቱ ወዳንተ በለመንሁ ጊዜ ይቅርታህን አታርቅብኝ የጌቶች ጌታ የንጉሶች ንጉሥ ሆይ ወደ አንተ የሚመላለሱትን ዕርቅ ትወዳለህና የሥጋና የነፍስን ደኅንነትንም ትወዳለህና፡፡

ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የቀናች ሃይማኖትንና እውነተኛ መመነስን ስጠኝ የጸራች ንስሐንም ትሰጠኝ ዘንድ እለምንሃንሁ፡፡የሚጠሉኝ ጠላቶቼ የክፉ አጋንንት ድንገት በሚመጡበት ጊዜ ወደ አድነኝ ነፍሴ ከሥጋዬ በምትለይበት ጊዜ ወደ አንተ አቅርበኝ እንጂ ካንተ ወደ ሌላ አሳልፈህ አትስጠኝ ሁሉ የሚቻልህ ፈጣሪ ሆይ ጠላቶቼን በኔ አታሠልጥናቸው አታሰናብታቸውም፡፡

ፈጣሪ ጌታ አዛኝ ይቅር ባይ ሆይ የይቅርታና የቅንነት ሣጥን እግዚአብሔር ሆይ ሕይወትን የምትሰጥ በጎ ነገርን የምትወድ አንተ ነህና ስለዚህ ከክፉ ጠላቶቼ አድነኝ እሳቸውን ከመፍራት የተነሣ ነፍሴ ትንቀጠቀጣለችና ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ያለክቡር ስምህና ያለ አንተ ለዘላለሙ ድኅነት የለኝም አሜን በእውነት፡፡

ውዳሴ አምላክ ዘሠሉስ

ስለ ሥጋ ወደሙ ቅዱስ ቍርባን
አምላኬ መድኃኒቴ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በዚህ በቅዱስ ቍርባን በሥጋ በደም መለኮት እንዳለህ አውቃለሁ። ይህንንም ስላወቅሁ ከክብር ሁሉ የከበረ ሥጋህን ከሰማያዊ ክብሩ ሁሉ ጋራ አከብርሃለሁ፤በዚህ በሚታየው ኅብስት መልክ እንድቀበል አምናለሁ። ከክብር ሁሉ የከበረ ደምህን ከሰማያዊ ክብሩ ሁሉ ጋራ አከብራለሁ፤ በዚህ በሚታየው ወይን መልክ እንድቀበል አምናለሁ፤ስግደት የሚገባው ግሩም መለኮትህንም እንድቀበል በፍጹም ልብ አምናለሁ። እንዲህም ከሆነ አንድ ቀን ፈጣሪዬን ጠባቂዬን ፈራጂዬን መድኃኒቴን እቀበላለሁ ዳግመኛም ይህንን ቅዱስ ቍርባን በኅብስትና በወይን አካል እንደማገኘው አምናለሁ፤ኅብስትና ወይን መሆን እንደሌለበትም አምናለሁ። የዓለም ሁሉ ፈጣሪ በመንግሥተ ሰማይ ኪሩቤል ሱራፌል የሚሰግዱልህ አንተ ነህ፤ ንጉሠ ነገሥት አንተ ተሠውረህበት እንዳለህ አውቄ አምኜ እቀበለዋለሁ። አምላኬ ሆይ ይህ ቃል እንደተናገርከው ነውና፤ ያንተ ቃል ነው እንጂ የሌላ ቃል አይደለም ያንተ ቃል ስለመሆኑ እናታችን ቤተ ክርስቲያን የምታምነውን ሁሉ አምናለሁ፤ እውነተኛ ምሥጢር አይደለም ለሚለኝ ነፍሴን ለሞት እሰጥበታለሁ። አምላኬ ሆይ እኔ የማይገባኝ የምድር ትል ስሆን አንተን አምላኬን ልቀበል እንዴት እችላለሁ። መላእክት የሚሰግዱልህ የዓለም ሁሉ ጌታ የሰዎች ሁሉ መሰብሰቢያ አንተ ነህ በአንተ ፊት ከንቱ ነገር የምመስል ነኝ፤ አንተ ግን ግሩም አምላክ ነህ፤እንዲህ ስትሆን አንተን ልቀበል እንዴት እችላለሁ።መቀበሌስ ይቆይና አንድ ጊዜ ስንኳ ዓይንህን መልሰህ ልታየኝ በእውነት የማይገባኝ ነኝ። ጌታዬ ሆይ አንተስ ከሰማይ የወረድህ ከኔ ጋር ልትገናኝ እኔን ደስ ልታሰኘኝ ሥጋህን ደምህን ልትመግበኝ መጣህልኝ። ነገር ግን ምንም አንተ እንዲህ ባለ ቸርነትህ ብትመጣልኝ እኔ ስለ ክፋቴ ብዛት አንተን ልቀበል በእውነት የማይገባኝ እንደሆንኩ አምናለሁ እታመናለሁ። ዳግመኛም እኔ ባንተ ፊት የተዋረድሁ ረብህ ጥቅም የሌለኝ ፍጡር ነኝ። ረብህ ጥቅም የሌለኝ ፍጡር ብቻ ስንኳ አይደለሁም። ሕግህን ያፈረስሁ ታላቅ ኃጢአተኛ ነኝ እንጂ፤ጌታዬ አንተ ታውቀኛለህና ምን እነግርሃለሁ? በአንተ ስንት ጊዜ ሸፈትሁ የሸፈትሁበትም ጊዜ ቍጥር የለውም። የነፍሴ ጌታ የነፍሴ ንጉሥ አንተ ብቻ ስትሆን በሽፍትነቴ ብዙ ጊዜ ከነፍሴ አስወጥቼ ሰድጄሃለሁ። በአንተ ቦታ ስለአንተ ፈንታ ያንተንና የኔን ጠላቶች ዛሬ አግብቼ አኑሬአለሁ፤አግብቼ ያኖርኋቸውም የአንተና የእኔ ጠላቶች ሰይጣንና ኃጢአት ናቸው። አንተ ግን ምሕረት ልማድህ ነውና እኔ እንዲህ ያለ ክፋት ሳደርግብህ እየኖርሁ ክፋቴን ሁሉ ሳታስብ በመሐሪነትህ ወደኔ ትመለሳለህ ዕድሜን ለንስሐ ትሰጠኛለህ። ራስህንም ሰጥተህ በነፍሴና በሥጋዬ ባለቤት ትሆናለህ ይህንንም ሁሉ ማድረግህ ለኔ ፍቅርህን ለማብዛት ብቻ ነው እንጂ ከኔ ትርፍ ነገር አገኛለሁ ብለህ አይደለም። ፍቅርህንስ ለማብዛት ካልሆነ ፍጥረትህ ሁሉ በአንተ ፊት ጻድቅ አይደለም፤የመላእክት ሁሉ ጻድቅነት ስንኳ የኔ ብቻ ቢሆን ጻድቅነቴን አስበህ አንተ ወደኔ ልትመጣ አይገባኝም ነበር እኔም አንተን ልቀበል የሚገባኝ አይደለሁም።ጌታዬ ሆይ አንተን የዘላለም ንጹሕ እንደሆንክ ሳውቅ አሁን በደካማ ልቤ በወስላታ አንደበቴ ክፋት አንድ ሰዓት ስንኳ በማይለየው ልቤ አንተን ልቀበል እንዴት እችላለሁ። ነገር ግን የማይገባኝ እንደሆንኩ አምናለሁ እታመናለሁ። ሰውን የፈጠርህ ሆይ በወሰንከው ሥርዓት ከፊትህ እቆም ዘንድ አጽናኝ ነፍስን የተከልክ አጽንቶችን ያለመለምክ ጌታዬ ሆይ የሥራዬን ክፋትና ኃጢአቴን አታስብ። ያፈርሁ የተዋረድሁ እኔ በፊትህ እፈራለሁና ወደ ይቅርታህ ትጠራኝ ዘንድ ተስፋህን አቆየኝ።

አቤቱ ስምህን ለካደ የሠራኸውን አስብ ከካደህ በኋላ ከገሃነም አውጥተህ ተድላ ወደሚደረግበት ወደ ገነት መለስከው፤ ተስፋውንም ካንተ አልቆረጠም፤ ችግረኛ የምሆን የኔን የክፉ በደሎቼን ሠውር የኃጢአቴንም መጋረጃ ቅደድ የፊቴን ጥቍረት በእውነተኛ የፍርድ ቀን መጻሕፍት በፊትህ በተገለጹ ጊዜ አታሳፍረኝ። አቤቱ በፍጥረትህ ሁሉ በምትፈርድበት ጊዜ በፊትህ ያፈርሁ የተጨነቅሁ አንደበተ ዲዳ ነኝና ከአንተ ልለምን ልማልድ አልደፍርም ስለዚህ አታሳፍረኝ። አቤቱ üእኔ ደስ አላሰኘሁህምና በፊትህም ጥቂት ስንኳ በጎ ነገር አላደረግሁምና በክፋቴ ብዛት በአእምሮዬ ማነስ አፌ ረክሳለች። ሸታለች እንጂ። በረከሰች አንደበቴ እናገራለሁ ያደፈ ፊቴንም ወደ አንተ አቀናለሁ ይቅር እንድትለኝ ወደ አንተ እለምን እማልድ ዘንድ እኔ ፍጥረትህ ነኝናበምታስፈራ በምታስደነግጥ በግርማ መለኮትህ በተገልጽህ ጊዜ ኃጢአትን ተመልቼ ከፊትህ ሳልቆም መላእክት አንተን ለማመስገን አንተን ለማድነቅ በወረዱ ጊዜ በገናና ስምህ ስላመኑ በመከራ በመገዛት የነበሩ ሰዎች ሁሉ ሕዋሳት ይሰበሰቡ ዘንድ በነጋሪት በተጠሩ ጊዜ ፍጥረትም ሁሉ የኃጢአት ሸክም ተሸክሞ በሚያስፈራ ዙፋንህ ፊት በሚቆሙበት ጊዜ የሠሩትን ክፉውንም በጎውንም ሁሉ ያን ጊዜ ሥራችን ይታወቃል። ምሥጢራችንም ይወጣል። መጋረጃችንም ይገለጣል። አቤቱ የኃሣራችንና የኃፍረታችን ደብዳቤ በመላእክት ፊት ይዘረጋል። ሥራችን ሁሉ በፍጥረት ሁሉ መካከል ይነበባል። አቤቱ ጌታዬ ሆይ የዚያች ሰዓት ግርማዋ ምን ያህል ይሆን፤ በሚያስፈራ በሚያስደነግጥ ዙፋንህ ተቀምጠህ በታየህ ጊዜ ክብርህም በፊትህ በተገለጠ ጊዜ የፈጠርከውን ፍጥረት በቅንነትና በእውነት በገዛህ ጊዜ የተሠወረውም ሁሉ በታየ ጊዜ ጻድቃንም ከኃጥኣን በሚለዩበት ጊዜ። አለኝታ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የመከራዋ ግርማ ሊያዩት ስለሚያስጨንቅ ስለዚያች ሰዓት ይቅርታህን እፈልጋለሁ። በፊትህ በሠራሁት ኃጢአቴ ከባሪያህ ጋር አትከራከር። በይቅርታህ ነው እንጂ ከፍርድህ መዳን የሚቻለው የለም። አቤቱ ጌታዬ መምህሬ ሆይ ከዚህች ከምታስጨንቅ ፍርድ አድነኝ። የሕይወት ያይደለ ፍርድ፤ ከሷ ስለመጣበት ሰው ሁሉ የሚጨነቅባት፤ አሁንም ጌታዬ ሆይ ነፍሴን ከዚያች ሰዓት ታድናት ከገሃነም ፍርድም ታድነኝ ዘንድ እለምንሃለሁ። በለጋስነትህና በቸርነትህ በርኅራኄህ ከወዳጆችህ ጋራ ትቆጥረኝ ዘንድ አሜን ይደረግልኝ። ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ እለምንሃለሁ ይቅርታህን በላያቸው ካፈሰስክ በመከራቸው ከወደድሃቸው ጋር ዕድል ትሰጠኝ ዘንድ ለእኔስ በፊትህ ለመቆም ለይቅርታህ የሚስማማ በጎ ሥራዬ አይታየኝም። በይቅርታህ እታመናለሁ እንጂ። በበጎ ሥራቸው ላገለገሉህና ለሚወዱህ ለነገርሃት ለዘላለም ደስታ በለጋስነትህ የበቃሁ ታደርገኝ ዘንድ ጌታዬ ሆይ የጠቆርኩ የረከስኩ እኔን ይቅር በለኝ። አቤቱ ምሳሌው ወደማይነገር ብርሃን አግባኝ፤ የጠቆረ ፊቴንም በእውነተኛ ንስሐ እሳት በፈላ ዕንባ እጠበኝ አሜን በእውነት ይደረግልኝ።

የዳዊት መዝሙር ፳፬

አምላኬ ሆይ ነፍሴን ወዳንተ አነሳሁ። አቤቱ ባንተ አምኛለሁና ለዘላለሙም አልፈር። ጠላቶቼም ደስ አይበላቸው በአንተ ያመኑ ሁሉ አያፍሩምና፣ዘወትር የሚበድሉ ግን ይፈሩ። አቤቱ መንገድህን አመልክተኝ ፍለጋህንም አስተምረኝ በቸርነትህም ምራኝ፤ አንተ ኃይሌ ነህ መድኃኒቴም ነህና እዘንልኝ፤ዘወትርም አንተን ተስፋ አደርጋለሁ አቤቱ ይቅርታህን አስብ፤ቸርነትህም ለዘላለም ነውና፤ ባለውቀቴና በልጅነቴ ጊዜ የነበረ ኃጢአቴን አታስብብኝ፤አቤቱ ስለ ቸርነትህ እንደ ይቅርታህ አስበኝ እንጂ፤ እግዚአብሔር ቸር ነው ቅንም ነውና ስለዚህ የሚስቱትን መንገድን ይመራቸዋል፤ለቅኖችም ፍርድን ያስተምራቸዋል፤ ለግሮችም መንገድን ያመለክታቸዋል ኪዳኑንና ምስክሩን ለሚጠብቁ፤የእግዚአብሔር መንገድ ይቅርታና እውነት ነው፤ አቤቱ ኃጢአቴ ብዙ ነውና ስለ ስምህ ይቅር በለኝ፤ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ማነው እሱም የመረጠውን መንገድ ይመራዋል፤ነፍሱም በመልካም ቦታ ታድራለች ዘሮቹም ምድርን ይወርስዋታል፤እግዚአብሔርን ለሚፈሩ ኃይላቸው ነው፤ ለሚጠሩትም እግዚአብሔር ምስክራቸው ነው። ሕጉንም ያስተምራቸዋል፤ዓይኖቼም ዘወትር ወደ እግዚአብሔር ናቸው፤ እሱ እግሮቼን ከወጥመድ ያወጣቸዋልና፤ወደ እኔ ተመልክተህ ይቅር በለኝ፤ብቸኛ ነኝ ችግረኛም ነኝና፤የልቤ ኀዘኑ ብዙ ነውና ከመከራዬ አድነኝ፤መከራዬንና ድካሜን እይ፤ኃጢአቴንም ሁሉ ይቅር በለኝ፤ጠላቶቼም እንዳይበዙ እይ፤ በግፍ ይጠሉኛል፤ነፍሴን ጠብቀህ አድነኝ፤ በአንተም አምኛለሁና አልፈር፤ፍጹምነትና ቅንነት ይጠብቁኝ፤ አቤቱ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁና፤እግዚአብሔር እስራኤልን ከመከራው ሁሉ ያድነዋል።

ውዳሴ አምላክ ዘረቡዕ

የንስሐ ጸሎት
አምላኬና ጌታዬ ሆይ አንተ ከኔ ከራቅህ እኔ አንተን ካልተቀበልሁ ሌላ ሕይወት አይገባኝምና አቤቱ እንዴት ባለ ገደል እወድቃለሁ ይሆን? እንደምንስ ባለ መከራ ተይዤ እጨነቃለሁ ይሆን? የልቤን ክፋት የልቤን ወስላትነት የሚያጠፋ መድኃኒት ካንተ ካላመጣሁ ከማን አመጣለሁ። ከጠላቶቼ የማመልጥበትን መማጸኛ ካንተ በቀር ማን አለኝ። የሰጠኸኝንስ ጸጋ በልቤ የሚያኖርልኝ ሌላ ማን አለ አንተ አይደለህምን። ኢየሱስ ሆይ አንተ የኔን ሥጋ ካልበላችሁ የእኔን ደም ካልጠጣችሁ በላንተ ሕይወት የለም አልህ። እንዲህም ካልህ በነፍሴና በሥጋዬ እንዳልሞት ይገባኛል ሳልል በግድ ወደ ቍርባን እቀርባለሁ። ዳግመኛም አንድ ክፉ ልጅ በረኀብ በተጨነቀ ጊዜ «እንደዚህ በረኀብ እንዳልሞት ተነስቼ ወደ አባቴ ልሂድ አባቴንም በድዬዋለሁና ከባሮችህ እንደ አንዱ አድርገኝ እንጂ ልጅህ ልባል አይገባኝም ልበል» ብሎ አስቦ ወደ አባቱ እንደሄደ አባቱም በሩቅ ባየው ጊዜ በርኅራኄ በፍቅር እንደተቀበለው ተናግረሃልና ሉቃ. ፲፭፥፲፩-፴፫

እኔ በዚህ ምክንያት እንደርሱ ሁሉ በእግረ ንስሐ ተነሥቼ ወደ አንተ ወደ ርኅሩኅ አባቴ እመጣለሁ፤ወደ አንተ ወደ ኃይሌ እመጣለሁ፤ ወደ አንተ ወደ ጠባቂዬ እመጣለሁ፤ ወደ አንተ ወደ መማጸኛዬ እመጣለሁ፤ ወደ አንተም አሥነስቶ የሚያመጣኝ «ኑ ብሉ ብለህ አስጠራኻቸው፤» በቀሩ ጊዜ በወንጌል የተናገርኸው ቃል ነው፤ ማቴ. ፳፪፥፩-፲፬ ዳግመኛም ወደ አንተ መምጣት እንዳልፈራ ልቤን የሚያጽናናልኝ እውቀቴንም የሚጨምርልኝ ከኔ ክፋት የሚበልጥ የአንተ መሐሪነት ነው። ፈሪሳውያንንም «ኃጢአተኞችንም ይቀበላል ከኃጢአተኞች ጋራ ይበላል» ቢሉህ ነቀፋቸውን ፈርተህ ኃጢአተኞችን መቀበል እንዳልተውህ ከእርሳቸውም ጋር መብላትን እንዳልተጸየፍህ በወንጌል ተጽፎ አለ። ማቴ. ፱፥፲-፲፫ ይህም እውነት ከሆነ የኃጢአተኞች አለቃ እኔ ነኝና ወደ አንተ ስቀርብ እንዳትጸየፈኝ አውቄ ብቀርብ በደምህና በሥጋህ ነፍሴንና ሥጋዬን ከኃጢአት እንድታነጻልኝ ተስፋ አለኝ። ልቤን እንደ እሳት የሚያቃጥለኝን ኃጢአት ሁሉ እንድታጠፋልኝ ተስፋ አለኝ። የቸርነትህ ድልብ አያልቅምና ለአንተ የምከፍልህን ዕዳ እንድትተውልኝ ተስፋ አለኝ። በለጋሥነትህ የከበርህ ነህና ልቤን ባለጸጋ የሚያደርግልኝ ጸጋ፤ ከገሃነመ እሳት የሚያድነኝ ጸጋ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚያገባኝ ጸጋ እንድትሰጠኝ ተስፋ አለኝ። አምላኬና ጌታዬ ሆይ፤ፈጣሪዬ ሆይ እለምንሃለሁ፤ ከኃጢአቴ ባሕር ማዕበል ታድነኝ ዘንድ ከመሰናክሌም፤ ደቀ መዝሙርህ ጴጥሮስን ከመዋረዱ ጽናትና ከባሕር ድንጋጼ እንደ አዳንኸው፤ ከፍ ከፍ ባለች ክንድህና በጸናች ቀኝህ ከመሠጠምም እንደ አዳንኸው፤ማቴ. ፲፬፥፳፰-፴፫

ሐዋርያህ ጳውሎስንም እንደተቀበልከው አንተን ከካደ ምዕመናንንም ከተጣላ በኋላ የዲያቆናት አለቃ የሰማዕታት መጀመሪያ እስጢፋኖስንም ለመግደል ከከተማ ከወጣ በኋላ ከዚህ ሁሉ በኋላ በቅዱሳንህ ጉባዔና በቤተ ክርስቲያንህ ዘንድ ለወገኖችህ በስምህ የሚያስተምር የከበረ ታላቅ መምህር እንዳደረግኸው። የሐዋ.ሥራ ፯፥፷ ፰፥፫ ፱፥፩-፴፩ ፲፫፥፪-፲፪ ፲፱፥፲፩-፳ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ እንደዚህ ሁሉ ከቤተ ክርስቲያን ሥርዓት የራቅሁ እኔን ተቀበለኝ ከይቅርታህም አታርቀኝ። ቸርነትህንም ለዘላለሙ አትንሳኝ።

ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የመፃጉዕን ኃጢአት ይቅር እንዳልኸው በሥልጣንህም ከሃሊነት በብዙ አሕዛብ ፊት ተግቶ አልጋውን ተሸክሞ እንዲነሣ እንደ አደረግኸው ዮሐ.፭፥፪-፱ እንደዚህም ሁሉ ኃጢአቴን ይቅር ብለህ ለኔ ለባሪያህ የሥጋና የነፍስን ሕይወት ስጠኝ። አባቴ ሆይ በክብር ስም ስለተጠራሁ በደኅንነቴ ወራት ሁሉ በጎ አገዛዝ እገዛልህ ዘንድ አምልኮትህን አጽናልኝ። ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ለዘላለሙ የምትኖር ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ አቤቱ የከነናዊትን ልመና እንደሰማህ ታማ ሥቃይ ጸንቶባት ከነበረች ከልጅዋ ጋኔን እንዳወጣህ «ሃይማኖትሽ ታላቅ ነውና እንደ ፈቃድሽ ይደረግልሽ» እንዳልኻት ፈውስንም እንደሠጠኻት ማቴ. ፲፭፥፳፩-፳፰ ጌታዬ ሆይ ጎስቋላ ችግረኛ የምሆን እኔንም እንዲሁ እለምንሃለሁ። ከንቱውንም ዓለም በመመኘት የሚከራከረኝ ሰይጣንን ከኔ ታርቀው ዘንድ በየጊዜ ሁሉ ፈቃድህን እንድሠራ በቸርነትህ ትረዳኝ ዘንድ አሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈሳት የነበርችውን ሴት እንደ አዳንካት በአንተ ስለ አመነች ከደዌዋ አድነህ ሕይወትን እንደሠጠኻት ማቴ.፱፥፳-፳፫ እንደዚህም ሁሉ እኔንም ከደዌዬ ፈውሰኝና ሃይማኖቴን ስጠኝ፤ ከኃጢአቴም አንጻኝ። በሕወቴም ወራት ሁሉ በእውነት አመልክህ ዘንድ ክቡር ስምህንም እስከ ዘላለም አስተምር ዘንድ። አሜን በእውነት። አቤቱ ፍጥረትህን ሁሉ ያሳደፈች ኋላ ወደ ጽሩይ ንስሐ የተመለሰች ዘማን ይቅር እንዳልኻት ስለመመለሷና ስለ ልቅሶዋ ስለ ሐዘኗም «ኃጢአትሽ ተሠርዮልሻል በፍቅር ሂጂ» እንዳልኻት ዮሐ. ፰፥፫-፲፩ አቤቱ እንደዚህ ሁሉ የበዛ የሚያቃጥል እንባን ስጠኝ። ባለሁበት ዘመን ሁሉ ከዓይኔ ይፈስ ዘንድ ምናልባት ከእድፌ ጥቂት ያጥብልኝ እንደሆነ። አቤቱ በቸርነትህም የፊቴን ጥቍረት ያነጻልኝ እንደሆነ ከወገኖችህም ወገን እንደማያውቅህ አድርጎ ከካደህ በኋላ በመመለሱና በመጸጸቱ፤ በመረረ ኀዘኑም ጊዜ የሐዋርያት አለቃ የሚሆን የጴጥሮስን ንስሓ እንደ ተቀበልክ በምዕመናንም ላይ እንደ አንተ ያለ አለቃ አድርገህ እንደ ሾምከው ቤተ ክርስቲያን የምትታነጽበት የሃማኖት መሠረት አድርገህ የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻ እንደ ሰጠኸው ማቴ. ፲፮፥፲፯-፳ አቤቱ እኔንም እንደርሱ ተቀበለኝ። በዘመኔ ሁሉ ወደ አንተ እመለስ ዘንድ እጸጸትም ዘንድ የሠራሁትንም ኃጢአት ይቅር ትለኝ ዘንድ ስለ ክቡር ስምህና ስለ መልካም ስምህ ይቅር በለኝ። የቀራጩንም ኃጢአት ይቅር እንዳልከው ሃይማኖቱን እንደ ተቀበልከው። ከፈሪሳዊ ይልቅ የተመረጠና የነጻ እንደ አደረግኸው ስለ ትሕትናውም እንደ አከበርከው ሉቃ. ፲፰፥፱-፲፬ ጌታዬ ሆይ ዘወትር በፊትህ በደሌን አምን ዘንድ የነፍሴን ትሕትና ስጠኝ። ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በመስቀል ላይ ሳለህ እውነተኛ የባሕርይ አምላክ እንደሆንህ ስለ አመነብህ ቀማኛውን እንደ ተቀበልኸው «ለሁሉም እንደ ሥራው ትከፍለው ዘንድ በምትመጣበት ጊዜ አቤቱ በቸርነትህ አስበኝ» ስለ አለህ ለሰው ሁሉ የምታዝን ይቅር ባይ ሆይ እንዲህ ባለህ ጊዜ «ዛሬ ከኔ ጋራ በገነት ትኖራለህ» አልከው በኃጢአቱ በመገደሉ በክፉ ሥራውም ቸል አላልከውም፤አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን የተዘጋ ገነትን ፈጥነህ ከፈትህለት እንጂ፤እሱ ካሰበው ይልቅ ፍጹም ጸጋን ባለሟልነትን ከአንተ ሰጠኸው። ሉቃ. ፳፫፥፵-፵፫ ኃጥእ በደለኛ የምሆን የእኔንም ሰውነት ለዘላለሙ ወደ ምኖርበት ወደ ሰፊ ይቅርታህ አግባት። ኃጢአቴን ይቅር በለኝ በደሌንም በይቅርታህ ተላለፈው። አሜን ይደረግልኝ።

የዳዊት መዝሙር ፴፯

አቤቱ በቍጣህ አትቅሠፈኝ በመቅሠፍትህም አትገስጸኝ ፍላጾችህ ወግተውኛልና እጅህንም አጽንተህብኛልና፤ ከቍጣህ ፊት የተነሣም ለሥጋዬ ጤና የለውም፤ ከኃጢአቴም ወገን የተነሣ ለአጥንቶቼ ደኅንነት የላቸውም፤ ኃጢአቴ ከራሴ ፀጕር በዝቷልና እንደ ከበደ ሸክምም ከብዶብኛልና፤ከስንፍናዬ የተነሣ ቍስሌ መገለ በሰበሰም፤ ጐሰቈልኩ ፈጽሜም አረጀሁ፤ሁልጊዜ በትካዜ እመላለሳለሁ ነፍሴ ስድብን ተመልታለችና፤ለሥጋዬም ጤና አላገኘሁም፤ ፈጽሜም ታመምኩ ባለመከራም ሆንኩ፤ከልቤ ትካዜም የተነሳ ጮህሁ፤ ምኞቴም ሁሉ በፊትህ ነው፤ልቅሶዬም ከአንተ አይሠወርም ልቤ ደነገጸችብኝ ኃይሌም ተወኝ፤ የዓይኔም ብርሃን ፈዘዘ፤ወዳጆቼም ባልንጀሮቼም ባለጋራ ሆኑኝ፤ ከበው ጎተቱኝ፤ዘመዶቼም ተስፋ ቆርጠው ተለዩኝ፤ሰውነቴን የሚሿት ሁሉ ተበራቱብኝ፤መከራዬን የሚሹም ከንቱ ነገርን ይናገራሉ፤በሽንገላ ሊያጠፉኝ ዘወትር ይመክራሉ፤እኔ ግን እንደማይሰማ ደንቆሮ ሆንኩ፤አፉን እንደማይከፍት ድዳም፤እንደማይሰማ ሰው ሆንኩ፤ በመላሱም እንደማይናገር፤አቤቱ በአንተ አምኛለሁና፤አቤቱ አምላኬ ስማኝ፤ የጠላቶቼ መዘበቻ አታድርገኝ እላለሁ፤ሰኰናዬም ቢሰናከል አፋቸውን ይከፍቱብኛል፤ እኔንስ ሊገርፉኝ አቆዩኝ፤ ቍስሌም ዘወትር በፊቴ ነው፤በደሌን እናገራለሁ፤ስለ ኃጢአቴም እቆረቆራለሁ፤ጠላቶቼ ግን ጤነኞች ሆነው ይበረቱብኛል፤ በከንቱም የሚሉኝ በዙ፤ስለ በጎም ክፋት የሚመልሱልኝ፤እውነት ነገርንም በመከተሌ ይጠሉኛል፤እንደ ርኩስ በድን ጣሉኝ፤ አቤቱ አምላኬ ሆይ አንተ አትጣለኝ ከኔም አትራቅ፤አቤቱ የመድኃኒቴ አምላክ ሆይ እኔ ወደ መርዳት ተመልከት።

ውዳሴ አምላክ ዘሐሙስ

የንስሐ ጸሎት
የማፈቅርህ አምላክ ሆይ በቤተ ክርስቲያን የቍርባን ሥርዓት ባደረግህ ጊዜ የፍቅርህ ብዛት የተገለጸ ነው፤ ነገር ግን ተገልጾልኝ ሳለ እንዲህ ላለ ፍቅርህ የሚገባ ፍቅር በኔ ልብ የለምና፤ እኔ መልካም ግብር የሌለኝ ታናሽ ፍጡር ስሆን አንተም ትርፍ ነገር የማትሻ ታላቅ ፈጣሪ ስትሆን ለኔ ምግብ እስክትሆን ድረስ ያደረግህልኝ ፍቅር እጅግ የሚያስደንቅ ሊናገሩት የማይቻል እንግዳ ነገር ነው። ዳግመኛም የኔ ልብ ይህንን ፍቅር እያወቀ እስከ ዛሬ ድረስ ከአንተ ጋራ ታላቅ ፍቅር አለማድረጉ እጅግ የሚያስጨንቅ ነው። ይህም ሲታወቅ ከዛሬ በፊት የሚረባኝን ነገር ትቼ የሚጎዳኝን ነገር እፈልግ ነበርሁና ለበጎነትህ ልክ መጠን የሌለው አንተን ስለ ፍጹም በጐነትህ ሳልወድህ ቀርቻለሁ። አንተንም ባለመውደድ እየኖርሁ አንተን አለአዋቂ አድርጌ በሰው ፊት ወዳጅህ ልምሰል።

ጌታዬ ሆይ አንተን የማይወድ ሰው ተስፋ የሌለው ፍጹም ድኃ ነው እላለሁና እንዲህ ባለ ድንቁርናዬ እጅግ አዝናለሁ። ከእንግዲህ ወዲህ ግን ስለ በጎነትህ ብዛት በምትሠጠኝ ዘመን ሁሉ በፍጹም ልቤ በፍጹም ነፍሴ በፍጹም ኃይሌ እወድሃለሁ። ቢሆንልኝስ የኔ ፍቅር በመላእክትና በጻድቃን ፍቅር ልክ ሆኖልኝ እንደርሳቸው ብወድ በወደድሁ ነበር። ነገር ግን ፍቅሬ እንደርሳቸው ፍቅር ባይሆንልኝ በመመኘቴ ምክንያት የእርሳቸው ፍቅር ስለ እኔ ይሁንልኝ። አምላኬና ጌታዬ ሆይ እስከ ዛሬ ድረስ ሳልወድህ የኖርሁ ብቻ አይደለሁም። በዚህ ዓለም ላይ ብዙ ክፋት ያደረግሁብህ ነኝ። ስለዚህ ባንተ ፊት ቁሜ በታላቅ ኀዘን ክፋቴ ብዙ ነው እላለሁ። ዳግመኛም ኃጢአት በሠራሁ ጊዜ ካንተ ፈቃድ ወጥቻለሁና ከፈቃድህ በመውጣቴ እጅግ አዝናለሁ። ከኀዘኔም የተነሣ እጅግ እንዳለቅስ ዓይኖቼ የእንባ ምንጭ ቢሆኑልኝ በወደድሁ። አእምሮም ያለው ሰው በኃጢአቱ ምክንያት የሚያዝነው ኀዘን ሁሉ በእኔ ልብ ቢከማች በወደድሁ። እንግዲህ እንደምትሠጠኝ ኃይል እንደ ችሎታዬ አዝናለሁ። በፊትህም ቁሜ ኃጢአቴንና ክፋቴን የኃጢአቴንም ምክንያት እረግማለሁ። ጸጋህንም አጋዥ አደርጋለሁ። እስከ ጊዜ ሞት ወደ ረገምሁት ኃጢአት አልመለስም። ከኃጢአት ምክንያት እጠበቃለሁ። ለሐዋርያት (ለደቀ መዛሙርቶችህ) እንደገለጽህ የአምላክዊ ቃልህንም ትርጓሜ ዐውቀው ወደማትመረመር መለኮትህ እውቀት እንደ ተመለሱ ጌታዬ ሆይ የልቡናዬንና የኅሊናዬን ዓይን አብራልኝ፤ ክቡራት መጻሕፍትን አውቅ ዘንድ፤አቤቱ የትርጓሜአቸውን ምሥጢር ተረድቼ ትዕዛዝህን እንድሠራ ፈቃድህን እንድፈጽም የዕውራን ዓይን አብርተህ የነፍስና የሥጋ ብርሃንን እንደሠጠኸው። ማቴ. ፱፥፳፯-፴፩ ዮሐ. ፱፥፩-፵፩ አቤቱ ለኔም እንደዚህ ያለ ስጦታን ስጠኝ፤ እውነተኛ ብርሃንንም አይ ዘንድ የልቡናዬን ዓይን አብራልኝ። አቤቱ ፈቃድህን ሠርቼ እንድፈጽም አድርገኝ።

ለምፅ የያዘውን የፈውስከው ያነጻኻው አንተ ነህ። ማቴ. ፰፥፪-፬ እኔንም እንደሱ ከአፍአዊውና ከውሳጣዊው ኃጢአት ለምፅ አንጻኝ። ጸሎቴንም አንጻልኝ ብሎ እንደለመነህና እንደ ሰገደልህ አንተም በቸርነትህ የጸሎቱን ዋጋ እንደ ሠጠኸው ጸሎቴም እንደዛ እንደ ለምጻሙ ጸሎት ትሁን። ማር. ፩፥፵-፵፬ አቤቱ ችግረኛ ጎስቋላ የምሆን እኔም ፈውስን ካንተ እሻለሁ። ጀርባዋ ለጎበጠች ሴት ወደ ምኵራብ በገባች ጊዜ እንዳዘንህላት ይህ ማሠሪያ ካንቺ ይቆረጥ ደዌያትም ካንቺ ይራቁ እንዳልካት ፈጥና ድና ከቃልህ ሥልጣንና ከጌትነትህ ሁሉ እንዳደነቁ ሉቃ.፲፫፥፲-፲፫ በቸርነትህ ከኃጢአቴ ማሠሪያ ፍታኝ ያለ ነውር በፊትህ እመላለስ ዘንድ፤ የቀና አካልንም ስጠኝ። ለዘላለም ከሞትና ከሲኦል ማሠሪያ የተፈታሁ ልሁን። አሜን ይደረግልኝ። የነቢዩ የዳዊትን ንስሐ እንደ ተቀበልከው ጽኑ አወዳደቅ ከወደቀም በኋላ በነቢዩ በናታን እጅ እንደ አነሳኸው፤እግዚአብሔር ይቅር ብሎኻል ባለውም ጊዜ ለሥርየቱ ምልክት እንደ ሰጠኸው። ሳሙ.ካልዕ ፲፪፥፩-፲፭

የጠፋሁ ችግረኛ የምሆን እኔንም እንደሱ ይቅር በለኝ ታላቅ ኃጢአቴንም አስተሥርይልኝ ከወደቅሁትም ጽኑ አወዳደቅ አንሣኝ። ያለ አንተ የሚያነሳኝ የለምና፤ እኔ ችግረኛ ነኝና፤ እንደ ናታን ከወደቅሁበት የሚያነሣኝ የለም። የናታን ጌታ ሆይ እኔ ግን በቸርነትህ እታመናለሁ ሰውነቴንም ከፊትህ እጥላታለሁ፤የነቢያትም የአማላጆችም ጌታ አንተ ነህና ከድቀቴ አንሣኝ። በደሌንም ተላለፋት፤ ስለ በደሌም ቸል አትበለኝ። አቤቱ ጌታዬና አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ዘመኔም እስኪፈጸም ከኃጢአት ጠብቀኝ። እድናለሁ የማለት ተስፋን የቆረጠ የሕዝቅያስን ጸሎት ተቀብለህ በኢሳይያስ ቃል ብዙ ዘመንም እንደሰጠኸው ኢሳ.፴፰፥፩-፮ ችግረኛ ለምሆን ለኔም እንዲሁ አድርግልኝ። ለዘላለሙ የምትኖር ሆይ ከዘላለሙ ጉዳትና ከኀጢአት ሞት አንስተህ ሞት በሌለበት በመንግሥተ ሰማያት ሕይወትን ስጠኝ። በሰው ልጅ ያልተሠራች ለዘላለም በምትኖር ጥፋት በሌለባት በላይኛይቱ ማደሪያ። ጌታዬ ሆይ ለዘላለሙ ከዚይ አልታኖረኝ እወዳለሁ። አሜን ይደረግልኝ። ከፀሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያዋ ያሉ የጻድቃንን የነቢያትን ጸሎት እንደተቀበልህ የጸሎታቸውን ዋጋ ለነፍሳቸውና ለሥጋቸው ሕይወት የዘላለም ተድላን እንደሠጠኻቸው አውቀውም ሳያውቁ ተችሏቸው ሳይቻላቸውም የሠሩትን የተሠወረውንና የተገለጸውን ኃጢአታቸውን ይቅር እንዳልኻቸው፤ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ችግረኛ የምሆን እኔንም የተገለጸውንና የተሠወረውን የሠራሁትን ኃጢአቴን ሁሉ ታቃልልልኝ ዘንድ ሥርየትን ከአንተ እሻለሁ። ታላቅም ቢሆን ታናሽም ቢሆን እኔንም ባሪያህን እንዳገለገሉህ አድርገኝ፤ አንተንም በምጠራበት ሁሉ ጸሎቴን ተቀበለኝ ከወዳጆችህም ጋራ በማያልፍ ደስታ በባለሟልነት እኖር ዘንድ የበቃሁ አድርገኝ። ለዘላለሙ አሜን ይደረግልኝ በእውነት።

የዳዊት መዝሙር ፶

አቤቱ እንደ ቸርነትህ ብዛት ማረኝ ይቅር በለኝ። እንደ ይቅርታህ ብዛት ኃጢአቴን ደምስስ። እጠበኝ ከኃጢአቴም አንጻኝ በደሌን እኔ ራሴ አውቀዋለሁና። ኃጢአቴም ዘወትር በፊቴ ነው። አንተን ብቻ በደልሁ። በፊትህም ክፉ አደረግሁ። በነገርህ እውነተኛ ትባል ዘንድ። በፍርድህም ታሸንፍ ዘንድ። በፍርድህም ታሸንፍ ዘንድ። እነሆ በኃጢአት ተፀነስኩ፤ እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ። እነሆ እውነትን ወደሃልና። የማይመረመር ጥበብህን ንገረኝ። በስምዛ እርጨኝ እነጻማለሁ፤ እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ እጠራለሁ። ኃሤትንንና ደስታን አሰማኝ፤ የሰበርካቸው አጥንቶች ደስ እንዲላቸው። ፊትህን ከኃጢአቴ መልስ። በደሌንም ሁሉ አጥፋ። አቤቱ ንጹሕ ልቡናን ፍጠርልኝ። የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ። ከፊትህ አትጣለኝ፤ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ አታርቀው። በማዳንህ ደስታን ስጠኝ። በጽኑ መንፈስም ደግፈኝ። ለበደለኞች መንገድህን አስተምራቸው ዘንድ፤ሕግህን የሚዘነጉም ወደ አንተ ይመለሱ ዘንድ። የመድኃኒቴ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ ከደም አድነኝ። መላሴም ጽድቅህን በመናገር ደስ ይለዋል። ከንፈሮቼን ክፈት አፌም ምስጋናህን ያወራል ብትወድስ መሥዋዕትንም በሰጠሁህ ነበር። የሚቃጠለውን መሥዋዕት አትወድም እንጂ። የእግዚአብሔር መሥዋዕት የዋህ ልቡና ነው። እግዚአብሔር ገርና ትኁት ልቡናን አይንቅም። አቤቱ በሞገስህ ጽዮንን አስጊጣት። የኢየሩሳሌም ቅጽሮችም ይታነጹ። እውነተኛውን መሥዋዕት መባውንም ቍርባኑንም በምትወድበት ጊዜ ያን ጊዜ ፍሪዳዎች በመሠዊያህ ይሠዋሉ።

ውዳሴ አምላክ ዘቀዳም

የቅዱስ መልአክ ጸሎት
የምትጠብቀኝ መልአክ ሆይ ዛሬ ወደ ቅዱስ ቁርባን የምቀርብ ነኝና ቁርባንም ስለ ክብሩ ብዛት የሚያስፈራ የሚያስደነግጥ ሥራት ነውና እጅግ እፋራዋለሁ ስለዚህ አንተ ተከተለኝ ጌታዬ የሚገባ ልመና እንድለምነው አንተ ጌታዬን እንዴት እቀበልሃለሁ ይሆን እንዳልል ለልቤ መንፈሳዊ እውቀትን አሳይልኝ፡፡የኔ ልብ ካንተ በዚህ ታቦት ዙርያ ከሚቆሙት ከባልንጀሮችህ ልብ ጋራ እንዲሆን የልብ ትሕትና የልብ ፍቅር አስተምረኝ፡፡የምትረዱ ቅዱሳን ሁሉ ተከተሉኝ ጠብቁኝ፡፡

ውዳሴ አምላክ

በአብ ስም በወልድ ስም በመንፈስ ቅዱስ ስም አምናለሁ፡፡መግደልና ማዳን በሚቻለው አመንሁ ሞትና ሕይወት በእጁ ባለ አመንሁ መንፈሳዊውንም ሕይወት በሚሰጠው አምናለሁ፡፡በኪሩቤል ላይ በተቀመጠው አምናለሁ፡፡ምድርን ባያት ጊዜ እስከ መሠረቷ እንድትንቀጠቀጥ በሚያደርጋት አምናለሁ፡፡

አዳምን ልጆቹንም በምሳሌው በፈጠራቸው አምናለሁ፡፡አዳምና ልጆቹንም ለማዳን በመምጣቱ አምናለሁ ከንጽሕት ድንግል ከእመቤታችን ሰው በመሆኑ አምናለሁ፡፡ እኔ ትንሣኤና ሕይወት ነኝ ባለው አምናለሁ፡፡

የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ በኔ ያመነ አይሞትም ቢሞትም እኔ አሥነሳዋለሁ ባለው አምናለሁ ለፍጥረቱ ሕይወትን በሰጠ አምናለሁ እኔ በአብ እኖራለሁ አብም በኔ ይኖራል ‹‹እኔና አብ አንድ ነን›› ባለው አምናለሁ ኃጥአንን ወደ ንስሓ ይጠራ ዘንድ በመጣው ለፍጥረቱም ኃይልና ሥርየትን በሰጠው አምናለሁ፡፡

በጽሩይ ልቡና የሚለምኑትን በርኅራኄው ብዛት በሚቀበላቸው አምናለሁ፡፡ሳይሣሣ በሚሰጥ አምናለሁ ሥጋ ያለውን ሁሉ ልመና ሰምቶ ተስፋ በማያስቆርጥ አምናለሁ፡፡

ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ይቅር በለኝ ፡፡ ይቅር ትለኝ ዘንድ ይቅርታህን አያለሁና ያለ አንተ ይቅር ባይ ባይኖር ጌታዬ ሆይ የቀኝ እጅህ ፍጥረት ነኝና ይቅር በለኝ በደለኛ ኃጥእ የነበርሁ እኔ ላገለግልህ መጥቻለሁና ይቅርታህና ርኅራኄህ የበዛ ፈጣሪ ይቅር በለኝ ፡፡ በፊትህ የበደልሁ እኔ በፊትህ ወድቄ አለሁና በጎነትህ የሰፋ ጌታዬ ሆይ ይቅር በለኝ የተጠመቁ ክርስቲያንንም ሁሉ ይቅር በላቸው፡፡

ጌታዬ ሆይ በርኅራኄህ ብዛት ይቅር በለኝ፡፡ጌታዬ ሆይ በቸርነትህም ብዛት ይቅር በለኝ፡፡

ለኃጢአቴ ሥርየት ስለ ሠራህልኝ ጥምቀቴ ይቅር በለኝ፡፡ ኃጢአታችን ሊሠረይበት እንበላው ዘንድ ስለ ሰጠኸን ስለ አምላካዊ ሥጋህ ይቅር በለኝ፡፡የዘላለም መድኃኒትና ይቅርታን ስለ ሰጠህባት ስለ ሐዲሲቱ ሕግ አቤቱ እኔን ባርያህን ይቅር በለኝ፡፡

ጌታዬ ሆይ ወደ ተወደደ ልጅዋ ይሰማል እንጂ ልመናዋ በማይነቀፍ ይቅር ባይ አማላጅ በምትሆን በእመቤታችን በአማላጃችን ይቅር በለኝ አቤቱ ጌታዬ ሆይ ስለ ኃጢአቴ ብዛት ይህን ካንተ ከመቀበል ምንም የበቃሁ ባልሆን ይቅር በለኝ፡፡የኃጢአቴንም ብዛት አትይ ያለ ንስሓ ኃጢአት የሚያስተሠርይ የለምና፡፡

የኃጢአቴን እድፍ ከይቅርታህ ብዛት ጋራ የምታጽብ አንተ ስለሆንክ፡፡ለጋስ ሆይ ቸር ሆይ ይቅር በለኝ፡፡ሰማይ ስንኳ በአንተ ዘንድ ንጹህ አይደለምና የመላእክት ጭፍሮችም በአንተ ዘንድ ንጹሐን አይደሉም፡፡ንጹሐን ባይሆኑ ከእርሳቸው ወገን ከመዓርጋቸው የተዋረዱ አሉና ስለዚህ የፍጥረት ጌታ ሆይ በአንተ ዘንድ ንጹሕ የለምና ይቅር በለኝ እላለሁ፡፡

ጌታዬ ሆይ ይቅር በለኝ ወራቴ በከንቱ አልቋልና ዘመኔም በከንቱ ተፈጽሟልና ወደ ሌላም ዘመን እንድመለስ ተስፋ የለኝም፡፡

ጌታዬ ሆይ ይቅር በለኝ ፡፡በዕዳ ተይዤ አለሁና ነፍሴን ከኃጢአት ማሰሪያ የማስፈታበት የበጎ ሥራ ገንዘብ የለኝምና ክፉ ሥራዬም በዝቷልና ጌታዬ ሆይ ይቅር በለኝ፡፡

እነሆ መከር ደርሷልና አጫጆችም ከራስጌዬ ቁመዋልና ጌታዬ ሆይ ይቅር በለኝ፡፡የወይን መቁረጫው ጊዜው ደርሷልና ወይኑ ግን ጮርቃ ነው አይረባኝምና ጌታዬ ሆይ ይቅር በለኝ፡፡እነሆ በማያፈራው ዕንጨት ሁሉ ምሳር ተቃጥቷል ክፉ ዕንጨት የተባለም አንተን የማገለግልበት በጎ ሥራ የሌለኝ እኔ ነኝና ጌታዬ ሆይ ይቅር በለኝ፡፡

እኔ ቸል ስል ሞት ደርሶብኛልና ጌታዬ ሆይ እዘንልኝ፡፡ለመንገዴ ስንቅ የለኝምና መንገዴም እጅግ የምታደክም ናትና ምክንያትም ምላሽም የለኝም ጌታዬ ሆይ ራራልኝ፡፡መልእክተኛ ወደኔ በመጣ ጊዜ እንዳያስቸኩለኝ ከዚህ ዓለም ለመሄድ የበቃሁ አይደለሁምና በሞት ስጨነቅ መንገድም የሚገኘኝን አላውቅምና ጌታዬ ሆዬ እኔን ግን ያንተን ረዳትነት ተስፋ አደርጋለሁ ያለ ይቅርታህም ተስፋ የለኝም ጌታዬ ሆይ ከርኅራኄህ አታሳፍረኝ በድሎ ወደ አንተ በንስሐ የተመለሰውን አታሳፍረውምና ከመሓሪነትህና ከስጦታህ አታሳፍረኝ ከበዛች ለጋሥነትህም፡፡

ጌታዬ ሆይ ከመመካት አድነኝ ከኩራት አድነኝ ከትዕቢት አድነኝ ልቡናን ከማሳደግ ራስንም ከፍ ከፍ ከማድረግ ከቅናትና ከቂም ከሐሜትም ከባልንጀራም መፍረድ አድነኝ፡፡

አቤቱ ጌታዬ ሆይ ከታናሹም ከታላቁም ኃጢአት ሰይጣን ከሚያሰራውም ሥራ ሁሉ አድነኝ፡፡ሥጋንም ደስ ከማሰኘት አድነኝ ፡፡ከጉዳትም አድነን፡፡ አቤቱ ከዳተኛ ወንጀለኛ ከሚሆን አምላካዊ ፍቅርንም ከሚጠላ ከባላጋራዬ ከዲያቢሎስ እጅ አድነኝ፡፡ጠላቴንም በእኔ አታሰናብተው ድል መንሣትንም አትስጠው ድል በነሣ ጊዜ በእርሱ ኃይል ድል እንደነሳኝ አድርጎ እንዳመካ ጌታዬ ሆይ በመዓልት በሌሊትም በጊዜው በየሰዓቱም ሁሉ ጠብቀኝ ከክፉም ከርኩስም ሕሊና ለሚያዋርዱና እንደ እሳት ከሚያቃጥሉም ተጠብቄ እንድኖር አድርገህ ትእግሥትን ስጠኝ በቦታዬም እንድኖር አድርገኝ ሌባ እንዳይሰርቀኝ ከቦታዬም እንዳያናውጠኝ ገንዘቡ ጠፍቶበት ከወንድሞቹ እንደተለየ እንደ ባዕድ እንዳያደርገኝ በጠላቶቼ ፊት አትግለጠኝ እንዳይስቁብኝና እንዳይዘባበቱብኝ የተሠወረ ኃጢአቴንም እንዳይገልጹብኝ በቦታዬ አጽናኝ እንጂ መልካም ፍሬንም እንደምታፈራ እንደ ሠሌን ሥር ጽናት በልቡና ጽናትና በነፍስ ዝምታ በቦታዬ ትከለኝ፡፡

አቤቱ ጌታዬ ሆይ የነፍሴን ነገር እያሰብኩ በኃጢአቴ አለቅስ ዘንድ ልቡናዬ እንዳይታወክ ነፍሴንም በመውጣት በመግባት ካንዱ ወደ አንዱ መዞርን እንዳታደርግ ይህም የሰይጣን ጦርነት ነው ዘመኔም በሥራ ፈትነትና በዙረት እንዳይፈጸም የዲያብሎስንም ኃይል ከሃሊነት ባለው ሥልጣንህ አጥፋው እኔ ባርያህ በሥራዬ ሁሉ ደካማ ነኝና አባትና እናት እንደሌሉት ሕፃን በየጊዜው ሁሉ ወደ አንተ አንጋጥጣለሁ ባል እንደሌላት እንደተዋረደችም ሴት ደዌውም እንደ ጸናችበት ድውይ በቁስል ላይ ቁስል እንደ ተጨመረበት የሚፈውሰውንም ባለመድኃኒት እንደሚሻ፡፡

መዝሙረ ዳዊት 85

1 አቤቱ፥ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል አድምጠኝም፥ ችግረኛና ምስኪን ነኝና።
2 ቅዱስ ነኝና ነፍሴን ጠብቅ አምላኬ ሆይ፥ አንተን የታመነውን ባሪያህን አድነው።
3 አቤቱ፥ ቀኑን ሁሉ ወደ አንተ እጮኻለሁና ማረኝ።
4 የባሪያህን ነፍስ ደስ አሰኛት፥ አቤቱ፥ ነፍሴን ወደ አንተ አነሣለሁና።
5 አቤቱ፥ አንተ መሓሪና ይቅር ባይ ነህና፥ ምሕረትህም ለሚጠሩህ ሁሉ ብዙ ነውና።
6 አቤቱ፥ ጸሎቴን አድምጥ፥ የልመናዬንም ድምፅ ስማ።
7 ትመልስልኛለህና በመከራዬ ቀን ወደ አንተ እጠራለሁ።
8 አቤቱ፥ ከአማልክት የሚመስልህ የለም፥ እንደ ሥራህም ያለ የለም።
9 ያደረግሃቸው አሕዛብ ሁሉ ይመጣሉ፥ አቤቱ፥ በፊትህም ይሰግዳሉ፥ ስምህንም ያከብራሉ
10 አቤቱ፥ ድንቅ የምታደርግ አንተ ታላቅ ነህና፥ አንተም ብቻህን ታላቅ አምላክ ነህና።
11 አቤቱ፥ መንገድህን ምራኝ፥ በእውነትህም እሄዳለሁ ስምህን ለመፍራት ልቤ ደስ ይለዋል።
12 አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ በልቤ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፥ ለዘላለምም ስምህን አከብራለሁ
13 ምሕረትህ በእኔ ላይ ታላቅ ናትና፥ ነፍሴንም ከታችኛይቱ ሲኦል አድነሃታልና።
14 አቤቱ፥ ዓመፀኞች በእኔ ላይ ተነሥተዋል፥ የክፉዎችንም ማኅበር ነፍሴን ፈለጉአት በፊታቸውም አላደረጉህም።
15 አቤቱ፥ አንተ ግን መሓሪና ርኅሩኅ አምላክ ነህ መዓትህ የራቀ ምሕረትህም እውነትህም የበዛ
16 ወደ እኔ ተመልከት ማረኝም ለባሪያህ ኃይልህን ስጥ፥ የሴት ባሪያህንም ልጅ አድን።
17 ምልክትንም ለመልካም ከእኔ ጋር አድርግ የሚጠሉኝ ይዩ ይፈሩም፥ አቤቱ፥ አንተ ረድተኸኛልና፥ አጽንተኸኛልምና።